በአዲስ አበባ 18ሺ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀት ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፈጠሩ ተገለፀ

አዲስ አበበ፤ የካቲት 02 2004/ዋኢማ/ – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ በተጠኑና አዋጭነት ባላችው የሥራ መስኮች 18 ሺ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀት ለስራ አጥ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠሩን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጌታችው ታደስ ለዋልታ እንደገለጹት በብርታ ብረት፣ ኮንስትራክሽን፣ ዕደ-ጥበብና ኮብል ስቶን እንዲሁም በጨርቃጨርቅ የሥራ ዘርፎች የተሰመሩ 18 ሺ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀት ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል።

ማህበራቱ እያደረጉ ያለውን እንቅስቃሴ ለመገምገም በተደረገው ሁሉን አቀፍ ግምገማ 180 ኢንተርፕራይዞች በሞዴልነት እውቅና እንዳገኙ የገለፁት አቶ ጌታችው ማህበራቱን የመደገፍና የማብቃት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

ለኢንተርፕራይዞቹ ከሚደረጉት ዘርፈ ብዙ ድጋፎች መካከል የገንዘብ ብድር አንዱ ነው የሚሉት አቶ ጌታችው ከሁለት መቶ ሺ ለሚበልጡ አንቀሳቃሾች አንድ ነጥብ አምስት ቢሊየን የሚጠጋ ብር ብድር ተሠራጭቷል ።በብድር ከተሰራጨው ብር ውስጥ ከ880 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ተመላሽ መደረጉንም ተናግረዋል።

በያዝነው የበጀት ዓመት ለ130ሺ ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥሩ ዘርፎች ተግባራዊ እንደሚሆኑ የተናገሩት አቶ ጌታቸው ቢሮው በአምስት አመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሠረት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የአቅም ግንባታና የገበያ ትስስር ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል።

በጥቃቅን እና አነስተኛ የስራ መስኮች ተሰማርተው ውጤታማ ከሆኑት ኢንተርፕራይዞች መካከል የአዝዋ አዲስ ብርታ ብርትና እንጨት ሥራ ሁለገብ የኮንስትራክሽ ስራዎች ስራ አስኪያጅ ወጣት ቴድሮስ በቀለ እንደሚናገረው ማንኛውም ሰው ተደራጅቶ ቢሰራ ተጠቃሚ ይሆናል። ማህበሩ በብድር ባገኘው 12ሺ ብር ካፒታል በመነሳት ዛሬ ከ 2 ሚሊየን ብር በላይ ሀብት ማፍራቱንም ተናግሯል።