በጸረ-ድህነት ትግሉ ላይ የተጀመረው ሁለንተናዊ ጥረት በወጣቶች ተሳትፎ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለፀ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 05 2004 /ዋኢማ/ – በጸረ-ድህነት ትግሉ ላይ የተጀመረውን ሁለንተናዊ ጥረት ዘላቂና ውጤታማ ለማድረግ ወጣቱን መሰረት ያደረገ ፈጣን የልማት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የህወሓሃት የስራ አስፈጻሚ አባል አምባሳደር አዲስአለም ባሌማ አስታወቁ።

የቂርቆስ ወጣቶችና የልደታ ክፍለ ከተማ የሴቶች ማህበራት ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/ የተመሰረተበትን 37ኛ ዓመት የልደት በዓል ትናንት በውይይት አክብረዋል።

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስራ አንድ ወረዳዎች በትግራይ ወጣቶች ማህበር ስር የተደራጁ ወጣቶችን በፌዴራል ትራንስፖር ባለስልጣን አዳራሽ ያወያዩት አምባሳደር አዲስአለም እንዳሉት በፀረ-ድህነት ትግሉ ላይ የተጀመረውን አገራዊ እንቅስቃሴ ዘላቂና ውጤታማ ለማድረግ መንግስት ወጣቱን መሰረት ያደረገ ፈጣን የልማት ስራዎችን እያካሄደ ነው።

የተጀመረውን ፈጣን የልማት ግስጋሴ በማጠናከር በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከድህነት ለመውጣት ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በተለይ ወጣቱ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ በልማቱ የበለጠ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።

በኮንስትራክሽን፣ በህንጻ ግንባታ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ መስኮች እየታየ ያለው አበረታች ውጤት ወደፊትም ሁሉንም ወጣቶች ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ለማከናወን የሚያስችል ስልት ተቀይሶ እየተሰራበት እንደሆነ ተናግረዋል።

በከተሞች አካባቢ ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖርና ወጣቱ የቁጠባ ባህሉን እንዲያሳድግም ጥረት እየተደረገ መሆኑን አምባሳደር አዲስአለም አመልክተዋል።

ወጣቱ ድህነትን ለማሸነፍ መንግሥት ያስቀመጠውን ትክክለኛ ልማታዊ አቅጣጫ ተጠቅሞ ራሱንና ቤተሰቡን የመለወጥ ሃላፊነት ይጠበቅበታል ብለዋል።

በትግራይ ክልል በትምህርት፣ በጤና፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ ፣ በመንገድ፣ በአሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ በመልካም አስተዳደርና በሌሎችም ዘርፎች የተከናወኑ ስራዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ መሆናቸውንም ለወጣቶቹ አብራርተዋል።

በተመሳሳይ በልደታ ክፍል ከተማ አስር ወረዳዎች ነዋሪ የሆኑ የትግራይ ሴቶች ማህበር አባላት ሴቶችም መንግሥት በነደፈው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ ሊያበረክቱ ስለሚችሉት ሚና ውይይት አድርገዋል።

የህዋሃት ማእከላዊ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሄር እንዳሉት ሴቶች በትጥቅ ትግሉ ወቅት ያደረጉትን ሁሉን አቀፍ ትግል በጸረ ድህነት ትግሉም ሊደግሙት ይገባል።

በአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፎች እያደረጉ ያሉትን ንቁ ተሳትፎ የበለጠ በማጠናከር ራሳቸውንና አገራቸውን ከድህነት ለማላቀቅ እያደረጉት ያለውን ሁለንተናዊ ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

የህወሓት 37ኛ አመት የምስረታ በዓል የፊታችን የካቲት 11 ቀን 2004 ዓ.ም በመላው አገሪቱ በተለያየ ዝግጅት ድምቀት እንደሚከበር የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።