አዲሱ የግል ድርጅቶች ሰራተኞች የጡረታ አዋጅ የግሉ ዘርፍ ሰራተኞችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፤ ጥር 05 2004 /ዋኢማ/ – አዲሱ የግል ድርጅቶች ሰራተኞች የጡረታ አዋጅ በግሉ ዘርፍ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች ለጡረታ ሲደርሱ ተገቢውን ዋስትና የሚያገኙበትን አሰራር ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑን የግል ድርጅቶች ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው በላይ ሰሞኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በአክሱም ሆቴል ባዘጋጀው የግማሽ ቀን የፓናል ውይይት ላይ እንደተናገሩት፤ አዋጁ በሀገሪቱ እያደገ የመጣውን በግሉ ዘርፍ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች ዘላቂ የማህበራዊ ዋስትናን ያረጋግጣል።

በቀደመው አሰራር የጡረታ ዋስትና የነበራቸው በመንግስት ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች ብቻ የነበሩ ሲሆን፤ አዲሱ የግል ድርጅት ሰራተኞች የጡረታ አዋጅ ግን በግሉ ዘርፍ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞችን በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ፕሮቪደንት ፈንድ ከበርካታ የማህበራዊ ዋስትና ማረጋገጫ መንገዶች አንዱ ነው፤ ነገር ግን በዘላቂነት ለሰራተኛው ዋስትና መሆን ያለመቻሉ ሰራተኞች ጡረታን ሊመርጡ የሚችሉበት ዋነኛው ምክንያት ነው ብለዋል።

በፓናል ውይይቱ አዲሱን አዋጅ በተመለከተ ከህብረተሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎችና በአሰሪና ሰራተኛው ላይ አዋጁን አስመልክቶ ግልፅ ያልሆኑ ነጥቦችን በማንሳት ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

በተለይ ስለ አዋጁ አፈፃፀም፣ ቀደም ብሎ በየድርጅቶቻቸው በፕሮቪደንት ፈንድ የታቀፉ ሰራተኞች በአዲሱ አዋጅ የሚታይበት ሁኔታና ስለጡረታ መዋጮ አሰባሰብ ከተለያዩ አካላት ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሌ በበኩላቸው፤ የአዋጁ የአፈፃፀም መመሪያ ለበርካታ ጥያቄዎች መልስ የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ቀደም ብለው በፕሮቪደንት ፈንድ ታቅፈው የነበሩና አብዛኛው ሰራተኛ በዛው ለመቀጠል የተስማማባቸው የግል ድርጅቶች ውስጥ ያሉና በጡረታ የመካተት ፍላጎት ያላቸው ሰራተኞች በምርጫቸው ወደ ጡረታ የሚገቡበትን አሰራር ዘርግቷል ብለዋል።

በመዋጮው አሰባሰብ በኩልም ለአሰራር ቅልጥፍና እንዲረዳ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በኩል እንደሚሆን የተገለፀ ሲሆን፤ የመድረኩ ተሳታፊዎችም ስምምነታቸውን ገልፀዋል።

የሚሰበሰበውን ገንዘብ በማስተዳደር ረገድም የሶስትዮሽ አሰራርን ያስተዋወቀው አዲሱ አዋጅ ከመንግስት፣ ከኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽንና  ከአሰሪዎች ፌዴሬሽን  ተወካዮች የተዋቀረ ቦርድ በኃላፊነት አስቀምጧል።

በፓናል ውይይቱ ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ከኢሰማኮ፣ ከአሰሪዎች ፌዴሬሽንና ከግል ድርጅቶች የተውጣጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።