የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ለኢትዮጵያ የ53 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2004 (ዋኢማ) – ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን 53 ሚሊዮን ዩሮ የሚገመቱ የልማት ስራዎች ለማከናወን ሶስት የድጋፍ ስምምነቶች ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱን የፈረሙት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር አቶ ሱፊያን አህመድና የአውሮፓ ህብረት የልማት ትብብር ዳይሬክተር ፍራንሴስካ ሞስካ ናቸው፡፡

ገንዘቡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማስፋፋት፣ ለብዙሃን ማህበራት የአቅም ግንባታ ለመስጠትና የመንግስትን የልማት ስትራተጂን ለመደገፍ ይውላል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር አቶ ሱፍያን አህመድ ድጋፉ ለታለመው አላማ እንደሚውል በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡

የሕብረቱ ኮሚሽን የልማት ዳይሬክተር ፍራንሲስካ ሞስካ በበኩላቸው የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡