በክልሉ በሚገኙ 1 ሺህ 2 መቶ 41 ትምህርት ቤቶች የኤድስ መረጃ ማዕከላት ተቋቋሙ

ሀዋሳ፤  የካቲት 11/ 2004  (ዋኢማ) –  በደቡብ ክልል በሚገኙ 1 ሺህ 241 ትምህርት ቤቶች የኤች አይ ቪ ኤድስ መረጃ ማዕከላት መቋቋማቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ ፡፡

ቢሮው ለዋልታ እንዳስታወቀው የመረጃ ማዕከላቱ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የተቋቋሙት በክልሉ በ14 ዞኖች እና በ134 ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ የመለስተኛና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው ፡፡

የመረጃ ማዕከላቱ መቋቋም ተማሪዎቹ ከኤች አይ ቪ ኤድስ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በቀላሉ በማግኘት እራሳቸውን ከበሽታው ለመጠበቅ እንደሚያስችላቸው የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ያለው አባተ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ቢሮው ማዕከላቱን በቁሳቁስ ለማጠናከር በኤች አይ ቪ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መጽሐፍቶች የጥናት ውጤቶች በራሪ መልዕክቶች በሲዲ የተዘጋጁ ትምህርታዊ ድራማዎች እና የመዝሙር ካሴቶችን በማቅረብ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ባለሙያው አስረድተዋል፡፡

በቀጣይ ተማሪዎቹን ከማዕከላቱ ያሚያገኟቸውን መረጃዎች ለወላጆቻቸው እና ከትምህርት ቤቶች ወጪ ለሚገኙ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚያካፍሉበት ሁኔታ የማመቻቸት ሥራዎች በየትምህርት ቤቶቹ አስተዳደር በኩል በመከናወን ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡

ቢሮው የመረጃ ማዕከላቱን ከማቋቋም ጎን ለጎን ለ 3 ሺህ 380 መምህራን እና ለ2 ሺህ 748 ተማሪዎች የህይወት ክህሎትና የማህበረሰብ ውይይት የአመቻቾች ስልጠና መስጠቱን አስረድተዋል ፡፡

በደቡብ ክልል በ 2003 የበጀት ዓመት በክልሉ በሚገኙ የጤና ተቋማት አማካኝነት ለ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሰዎች   የኤች አይ ቪ ኤድስ ምርመራና የምክር አገልግሎት መሰጠቱን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያውን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ፡፡