75ኛው ዓመት የየካቲት 12 የሰማዕታት ቀን እየታሰበ ነው

አዲስ አበባ፤  የካቲት 13/2004 (ዋኢማ) – በፋሽስት ኢጣሊያ በግፍ የተጨፈጨፉ ኢትዮጵያውያን የሚታሰቡበት 75ኛው ዓመት የየካቲት 12 የሰማዕታተ ዕለት ዛሬ በመላው አገሪቱ እየታሰበ ነው።

ዕለቱን ምክንያት በማድረግ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታውና የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ተወካይ የመታሰቢያ ጉንጉን አበባ አኑረዋል ።

አበባ ባስቀመጡበት ወቅት አቶ አባተ እንደተናገሩት የአገራቸውን ሉዓላዊነት መደፈር በመቃወም በግፍ የተሰዉት ከ30ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ምንጊዜም ይታወሳሉ ብለዋል።

ጀግኖች አባቶቻችን ጠላትን በጦርነት አሸንፈው በክብር እንዳቆዩልን ሁሉ፤ የጊዜያችን ግንባር ቀደም ጠላት በሆነው ድህነት ላይ መዝመት እንደሚገባ አሳስበዋል።በዚህም ልማትና መልካም አስተዳደርን የላቀ ደረጃ ማድረስ እንደሚኖርብን አስገንዝበዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት አርበኞች በሰጡት አስተያየት ወጣቱ ትወልድ አገሩን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል ታሪክ መሥራት እንደሚጠበቅበትም አሳስበዋል።

የየካቲት 12 የሰማዕታት ቀን የሚታሰበው በ1929 ዓ.ም አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ኢትዮጵያውያን በወረወሩት የእጅ ቦምብ የፋሽት ጄኔራል የነበረውን ሩዶልፎ ግራዚያኒ ባቆሰሉት ወቅት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንዲጨፈጨፉ በሰጠው ትዕዛዝ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።

ንፁሃን ኢትዮጵያውያን በየመንገዱና ከየቤታቸው እየተጎተቱ ከመጨፍጨፋቸው በላይ ብዙዎች በመኖሪያ ቤታቸው እንዳሉ በር በላያቸው ላይ እየተዘጋ ተቃጥለዋል። 4 ሺህ የሚሆኑ መኖሪያ ቤቶችም ወደ አመድነት መቀየራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።