ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ አንድ ሺ ጥንዶች በጋራ የጋብቻ በዓላቸውን ሊያከብሩ ነው

አዲስ አበባ የካቲት 15/2004 (ዋኢማ) – ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ለተውጣጡ አንድ ሺ ጥንዶች በመጪው ሰኔ ጋብቻቸውን በአዲስ አበባ ከተማ በደመቀ ሁኔታ በጋራ ለማክበር ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ኤሚነንስ ሶሻል ኢንተርፕርነርስ አስታወቀ።

የኢንተርፕርነርሱ ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋዬ አለሙ ዛሬ በራዲሰን ብሉ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣ መግለጫ፤ የጋብቻ ፕሮግራሙ የጥንዶቹን የተንዛዛ የጊዜና የገንዘብ ብክነትን ከማዳኑም ባሻገር የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን የጋብቻ፣ ባህልና ወግ በማስተዋወቅ በኩል ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል።

የጋብቻ ፕሮግራሙ ጥንዶቹ በተለያዩ የማህበረሰባዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ያለመመቻቸት የተነሳ ጋብቻቸውን መፈፀም ያቃታቸውን በመደገፍ ወደ ጋብቻ እንዲሄዱ ለማድረግ ነው።

ጋብቻው የሚካሄደው “የሺህ-ጋብቻ-2004” በሚል መሪ ቃል ሲሆን፤ የሰርግ ስነ-ስርዓቱ በሚሊኒየም አዳራሽ ሊካሄድ እንደሚችል ተጠቁሟል።

“የሺ ጋብቻ – 2004ን” ስኬት በጊነስ ወርልድ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ ለማስመዝገብም ጥረት እንደሚደረግ የተገለፀ ሲሆን፤ ይህም የሀገሪቱን በጎ ገፅታ ከመገንባት አንፃርና ማህበረሰቡን እርስ በርስ በማስተዋወቅ በኩልም ከፍተኛ ሚና ይጫወታል በማለት ተናግረዋል።

ፕሮግራሙ ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሙሉ ትብብር ማግኘቱን አቶ ተስፋዬ ገልፀው፤ ስለ ፕሮግራሙ ከተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የግል ባለሀብቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ጋርም የምክክር መድረክ መካሄዱን ተናግረዋል።

የኤችአይቪ/ቫይረስ በደማቸው ያለባቸው ወገኖችና በጤናና በገንዘብ እጥረት ምክንያት ጋብቻቸውን ሳይፈፅሙ ለቀሩ ጥንዶች እድሉ እንደሚሰጥም በመግለጫው ወቅት ተገልጿል።