የጣሊያን አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር በጋራ የመስራት ፍላጎት አላቸው

አዲስ አበባ, የካቲት 17 ቀን 2004 (አዲስ አበባ) – የኢትዮጵያ የእድገትና የትራንፎርሜሽን እቅድን በመከተል በአገሪቱ ከሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ጋር የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ የሚያስችል አጋርነት ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ኮንሶርዚዮ ኢታሊ የተባለ የጣሊያን አነስተኛና መካከለኛ ኩባንያዎች ጥምረት አስታውቋል፡፡

የጣሊያን የውጭ ንግድ ኢንስቲትዩት በበኩሉ በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ከ24 በላይ የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል ብሏል፡፡

የኮንሶርዚዮ ኢታሊ ፕሬዚዳንት ሚስተር ፋቢዮ ሳንቶኒ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አንዳስታወቁት የኢትዮጵያ የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ የአገር ውስጥ ምርት ጥራት ደረጃን በማሳደግ በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ ድርጅቶችን ለመፍጠር መሰረት የሚጥል በመሆኑ አድናቆት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

የጣሊያን ኩባንያዎችም የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር መፍጠር በሚያስችሉ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ በአጋርነት የመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው ብለዋል፡፡

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ የጣሊያንን ምርቶች በውጪው አለም ገበያ ተፈላጊ እንዲሆን ካደረጉት ኩባንያዎች ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ናቸው፡፡

ከዚህ ልምድ በመነሳት በመካከለኛና አነስተኛ የማምረቻ ዘርፎች የሚሰማሩ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን በጥራት ማምረት ከቻሉ ገበያ የማግኘት ችግር አይገጥማቸውም ብለዋል፡፡

ይህን ለማሳካትም በዘርፉ ልምድ ያላቸው አለም አቀፍ ተቋማት ወደ ታዳጊ አገራት ሲገቡ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ለማድረግ በሚያስችላቸው መልኩ ከአገራቱ ባለሙያዎች ጋር መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት ሚስተር ፋቢዮ፡፡

በተደጋጋሚ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየተመዘገበ ያለው የኢኮኖሚ እድገትና የተፈጠሩት የትብብር አጋጣሚዎች ለውጭ ባለሃብቶች ሳቢና አመቺ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብለዋል፡፡

ኮንሶርዚዮ ኢታሊ ከአግሮ ፉድ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ እስከ ታላላቅ በመንገድና በግድብ ግንባታ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎችን ያቀፈ የዘጠኝ ድርጅቶች ጥምረት መሆኑን ተናግረው እነዚህ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰማሩባቸው ሰፊ ዕድሎች እንዳሉ መጠናቱንም ጠቁመዋል፡፡

ኢንቨስትመንት አትራፊነት ብቻ ሳይሆን እሴት ፈጣሪ መሆን አንደሚገባው እናምናለን የሚሉት ሚስተር ፋቢዮ በዚህ ረገድ የወከሏቸው ድርጅቶች ኢትዮጵያን በቀላሉ መገኘት በሚችሉ የኢንዱስትሪ ጥሬ እቃዎቿ፣ በሰው ሃብቷና የመፍጠር ብቃት ባላቸው ባለሙያዎቿ የተነሳ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት እንደሚመርጧት ነው የገለጹት፡፡

የጣሊያን ኩባንያዎች ልምድ ባዳበሩባቸው በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ ኢንዱስትሪና በግብርና ምርቶች ዘርፍ በኢትዮጵያ ውስጥ ሊያከናውኑት የሚችሉት መጠነ ሰፊ ስራ እንዳለ መረዳታቸውን ፕሬዚዳንቱ ገልጸው ይህን ተግባራዊ ለማድረግም ጥምረቱ አዲስ አበባ ውስጥ ቢሮ መክፈቱን አስታውቀዋል፡፡

ቢሮው እነዚህ ኩባንያዎች ሊሰማሩባቸው የሚችሉባቸወን የስራ ዘርፎች ከማጥናትና ከመለየት ባሻገር ከጣሊያን ኩባንያዎች ጋር በጋራ መስራት ለሚፈልጉ አገር በቀል አምራች ድርጅቶችም ሁኔታዎችን እንደሚያመቻችና በቂ መረጃ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡

አንደኛ ድምጽ መግቢያ 0፡38 ‘’የጣሊያን አነስተኛና መካከለኛ ኩባንያዎች በ2011 ታንዛኒያን ሞዛምቢክን፣ካሜሮንን፣ቻድን፣ጋናንና ሴኔጋልን ጎብኝተናል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ከነዚህ አገራት በተሻለ ለነዚህ ኩባንያዎች ምቹ የምትሆንባቸው ብዙ ምክንያቶች እንዳሉም ተረድተናል፡፡ በኢትዮጵያ እድገት አለ፡፡ ጥሬ እቃ አለ፡፡ የግሉ ዘርፍ የሚበረታታበት አሰራር አለ፣ከሁሉም በላይ አገሪቱ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ያለቸው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የአገር ውስጥ ምርትን ያበረታታል፡፡ይህን ሁሉ በሌሎች ሃገራት ማግኘት አልቻልንም፡፡ ስለሆነም በኢትዮጵያ መስራት ምርጫችን ነው፡’’ መውጫ 1፡39

ሚስተር ፋቢዮ እንዳሉት የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ሙአለንዋያቸውን በስራ የሚያውሉት በቴክኖሎጂና በእውቀት ሽግግር ላይ ተመርኩዘው ነው፡ ፡ይህ ከሆነ ይላሉ ፕሬዚዳንቱ ‘’ማንም ተጎጂ የማይሆንበት የጋራ ተጠቃሚነት ተፈጠረ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በእምነትና በአንድነት ለረጅም ጊዜ በትብብር ለመስራት መሰረት ይጥላል፡፡’’ ብለዋል፡፡

የጥምረቱ አባላት ከሆኑት ኩባንያዎች አንዱ የሆነውና ኢምፕሬሳ ቶማት የተባለ በኮንስትራክሽንና ሲቪል ስራዎች ላይ የተሰማራ ኩባንያ ፕሬዚዳንት የሆኑት ሚስተር ኢዲ ቶማት በበኩላቸው እንደተናገሩት ኩባንያቸውን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የመጀመሪያቸው ነው፡፡

በአገሪቱ በመካሄድ ላይ ባለው ከፍተኛ የመሰረተ ልማትና የህንጻ ግንባታ ስራ መደነቃቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዘርፍ ላይ ኩባንያቸው ተሳታፊ እንዲሆን የሚፈልጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ኩባንያቸው በብዙ የአለም አገራት በተለያዩ የግንባታ ዘርፎች ላይ ተሰማርቶ መቆየቱን የገለጹት ሚስተር ቶማት ወደ አፍሪካ ገበያ ለመግባት ሲሞክሩ ይህ የመጀመሪያቸው መሆኑንና ኢትዮጵያን የመረጡበት ምክንያትም አገሪቱ በማደግ ላይ ያለችና ለውጭ ኩባንያዎች አመቺ የስራ ቦታ መሆኗን በመገንዘባቸው እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ለብረት ኢንዱስትሪዎች የሚያገለግሉ ማሽኖችን በማቅረብ ስራ ላይ የተሰማራው ፔርት የተሰኘ ኩባንያ የንግድና የፋይናንስ ኃላፊ ሚስስ ፍላቪያ ባሊኮ እንዳሉትም ኩባንያቸው ላለፉት ሁለት ዓመታት በዚህች አገር ሲሰራ የገጠመው አንዳች ችግር የለም፡፡

’’ኢትዮጵያ ለማንኛውም ኢንቨስትመንትና ንግድ የተመቻቸች አገር ናት፡፡ ይህቺ አገር በዚህ እድገቷ ከቀጠለች የአፍሪካ ኃያል አገር መሆኗ አያጠራጥርም’’ ብለዋል፡፡

የጣሊያን የውጭ ንግድ ኢንስቲትዩት የዓለም አቀፍ ኢንዱስትሪ ትብብርና ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ሚስስ ማሪኔላ ሎዶ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ከ24 በላይ የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው በቅርቡ ገልጸዋል ብለዋል፡፡

እንደ ኃላፊዋ ገለጻ በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማሳደግ ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን አያካሄደ ይገኛል፡፡

ሁለተኛ ድምጽ መግቢያ 2፡14 “ከሁሉም በፊት በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል ያለው ዘመናትን ያስቆጠረው ግንኙነት፣ አገሪቱ ያላት አመቺ የኢንቨስትመንትና የውጪ ንግድ ፖሊሲዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከጣሊያን አዲስ አበባ የሚያደርገው እለታዊ በረራ የጣሊያን ባለሃብቶች በዚህች አገር መዋዕለ ንዋያቸውን በስራ ላይ እንዲያውሉ የሚስቧቸው ነገሮች ናቸው ብዬ አምናለሁ’’ መውጫ 2፡50

ጣሊያን ውስጥ ለሁለት ቀናት የሚቆይ የኢትዮጵያና የጣሊያን ኩባንያዎች የቢዝነስ ፎረም ከመጪው መጋቢት 2 እስከ መጋቢት 4 እንደሚካሄድ የጠቆሙት ኃላፊዋ ለዚህም በከፍተኛ ባለስልጣናት የሚመራ የኢትዮጵያውያን የባለሃብቶች የልዑካን ቡድን ወደ ሮም እንደሚጓዝ አመልክተዋል፡፡

ይህ ፎረም የሁለቱን አገራት የንግድ ግንኙነት ከማጠናከሩ ባሻገር የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር በሚደረግባቸው ጉዳዮች ላይ ይመክራል ነው ያሉት ሚስስ ማሪኔላ፡፡

“በቅርብ ቀናት ኢትዮጵያ ውስጥ ባካሄድነው የቢዝነስ ሴሚናርና ጥምረት መፍጠሪያ ውይይት እንዲሁም ጣሊያን ውስጥ በቅርቡ በሚካሄደው የአገራቱ የቢዝነስ ፎረም በጣሊያንና በኢትዮጵያ መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያስገኝ የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት እንደሚፈጠር ተስፋ እናደርጋለን ” ነው ያሉት ሚስር ማሪኔላ፡፡