ሀገራዊ ትግሉን በብቃት ለመወጣት ስልጠና አንዱ መንገድ እንደሆነ ኢህአዴግ አስታወቁ

አዲስ አበባ፤ የከየካቲት 26/2004 (ዋኢማ) – አገራችን ለሚታካሂደው ዘርፈብዙ ትግል የአመራር አባላት ስልጠና ወሳኝ መሆኑን ኢህአዴግ አስታወቀ፡፡

የኢህአዴግ የስልጠና  ዘርፍ ሀላፊ አቶ መንግስትአብ ገ/ኪዳን እንደገለጹት    በሶስት የስልጠና ጣቢያዎች ላይ መሰጠት የጀመረው የኢህአዴግ ኮር መካከለኛ አመራር አካላት ስልጠና በአገሪቱ የተጀመረውን ሁለንተናዊ እድገት ለማስቀጠል አንደኛው መንገድ መሆኑን የኢህአዴግ የሥልጠና ዘርፍ ሀላፊ አቶ መንግስትአብ ገ/ኪዳን ገለጹ፡

ኢህአዴግ አምስት ሺህ አምስት መቶ ለሚሆኑ በወረዳ ካቢኔ ደረጃ ለሚገኙ መካከለኛ አመራር አካላት ለአንድ ወር ተኩል እየሰጠ ያለው ስልጠና በብርሸለቆ፣ ጦላይ እና በቆጂ የስልጠና ጣቢያዎች በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ስልጠናው በተከታታይ ለሁለት ዙር የሚሰጥ ሲሆን ስልጠናው ከተጠናቀቀ በኃላ እንደ አስፈላጊነቱ ቀጣይ ዙሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡

ስልጠናውን መስጠት ያስፈለገበትን ምክኒያት አቶ መንግስትአብ ሲያስረዱ አመራሩ የተነደፈውን የህዳሴ መስመር በአስተማማኝ ሁኔታ ለማሳካት በሚደረገው ርብርብ አደናቃፊ የሆኑ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችን ለይቶ ለመታገል እንዲሁም በጎ ተፅዕኖዎችን አሟጦ ለመጠቀም የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን እንዲገነዘብ እና ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮችን በተገቢው መንገድ ጨብጦ የሕዝቡን ጥያቄዎች በአግባቡ በመመለስ አገሪቱን  መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው አገሮች ደረጃ ለማድረስ እንዲቻል ብቃት ያለው አመራር ተገቢ መሆኑንና ለዚህም የአቅም ግንባታ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ይሄ ስልጠና ለአመራሩ እንዲዘጋጅ ተደርጓል ብለዋል፡፡

የሥልጠና ዘርፍ ሀላፊው አቶ መንግስትአብ ከዚህ በፊት ኢህአዴግ በአራት ዙር ለሁለት ሺህ ሁለት መቶ ከፍተኛ የአመራር አባላት ስልጠና መስጠቱን አስታውሰው የአመራር አባላቱ በስልጠናው የተገኙትን መልካም ልምዶች የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚጠቀሙባቸውና ያላቸውን እውቀትና ጉልበት በማስተባበር ለሀገሪቱ ህዳሴ የሚጠበቅባቸውን መስዋዕትነት እንደሚከፍሉ፤ ኪራይ ሰብሳቢነትና መገለጫዎቹ እንዲወገዱ ለማስቻል አገራዊና ወገናዊ ግዴታቸውን እንደሚወጡም ሰልጣኞቹ ስልጠናቸውን ሲያጠናቅቁ ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡