28 ታዳጊዎች ከታንዛኒያ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ

ሰኔ 22/2013 (ዋልታ) – በህገወጥ ስደት ወደ ደቡብ አፍሪካ ለሚደረግ ጉዞ ከአገር ወጥተው የታንዛኒያን ድንበር ጥሰው ሲገቡ በአገሪቱ ፖሊስ ተይዘው የነበሩ 28 ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡

ታዳጊዎቹ ከሌሎች 36 እድሜያቸው ከ18 አመት በላይ ከሆኑ ስደተኞች ጋር ተይዘው የነበሩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ይህን ተከትሎ የታንዛኒያ መንግስት እድሜያቸው አነስተኛ የሆኑትን ለማሰር የማይችል በመሆኑ በአፋጣኝ ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ኤምባሲው ሁኔታውን እንዲያመቻች ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የተመለሱ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በታንዛኒያ እስር ቤቶች ታስረው ያሉ በመሆኑ ሁሉንም ዜጎች ወደ አገር ቤት ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ኤንባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡