የኢህአዴግ ም/ቤት አባላትና ሌሎች የሚመለከታቸው ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ያለፉት 15 አመታት የተሃድሶ ጉዞ ግምገማ መጀመሩን የኢህአዴግ ም/ቤት ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
በዚህ የግምገማ መድረክ ያለፉትን 15 አመታት የተሃድሶ ጉዞ በጥልቀት በመገምገም የተመዘገቡ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በህዝባዊ የአላማ ጽናት ታግሎ በማረም የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ አጠናክሮ የማስቀጠል ጉዳይ ትኩረት እንደሚሰጠው ተገልጿል፡፡
የኢህአዴግ ም/ቤት ከድርጅቱ ጉባኤ ቀጥሎ ከፍተኛው የስልጣን አካል በመሆኑ በኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቀረበለት የ15 አመታት የተሃድሶ ጉዞ ግምገማ መነሻነት ጥልቀት ያለው ግምገማ በማካሄድ የሚታዩ ችግሮችን መሰረታዊና ስር ነቀል በሆነ ሁኔታ ለመፍታት የሚያስችሉ ውሳኔዎችን እንደሚያስተላልፍም ይጠበቃል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ም/ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው የሁለተኛው የአምስት አመት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ የመጀመሪያው አመት አፈጻጸምን ይገመግማል። በዚህም በ2008 በጀት አመት የታዩ ጥንካሬዎችና መልካም አፈጻጸሞች ተጠናክረው የሚቀጥሉበትን እንዲሁም ደካማ አፈጻጸሞችና እጥረቶች የሚታረሙበትን አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል።
ምክር ቤቱ በ2009 የበጀት አመት የድርጅትና የመንግስት እቅድ ላይ ተወያይቶ የሚያጸድቅ መሆኑንም የኢህአዴግ ም/ቤት ጽ/ቤት በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡