በአገሪቱ በአራት የታዳጊ ክልሎች የሚገኙ ከ1ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ አርብቶ አደሮች የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የፌደራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የተመጣጣኝ ልማት የማረጋጋጥ ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሳሙኤል ንጉሴ ለዋልታ እንደገለጹት ከ2003 ጀምሮ ልዩ ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው በአፋር፣ሶማሌ፣ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የሚገኙ ከ 1ነጥብ9 ሚሊዮን በላይ አርብቶ አደሮች በመደንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም እንዲታቀፉ በማድረግ የተለያዩ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ።
በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 89 ንዑስ 4 ላይ በልማትና በዕድገት ወደ ኋላ የቀሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ልዩ ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በተደነገገው መሠረት በአራቱ ክልሎች የሚገኙ አርብቶ አደሮችንና ከፊል አርብቶ አደሮች የጤና፣ የትምህርት፣ የመጠጥ ውሃና መንገድ አገልግሎቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን አቶ ሳሙኤል አመልክተዋል ።
በአራቱም ክልሎች ለረጅም ጊዜ ሲስተዋል የነበረውን የምግብ ዋስትና ችግር ለመፍታት መንግሥት ትኩረት በመሥጠት አርብቶ አደሩ በመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራሙ እንዲሳተፍ ሲደረግ መቆየቱን የጠቆሙት አቶ ሳሙኤል አርብቶ አደሩ በግብርናው ዘርፍ ከመሳተፍ ባለፈ የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂ ግብዓቶች ቀርበውለት ምርትና ምርታማነቱ እያደገ መሆኑን አስረድተዋል ።
ከ2003 እስከ 2007 ዓም ብቻ በአጠቃላይ በአራቱም ክልሎች 562 መንደሮች ተቋቁመዋል ያሉት አቶ ሳሙኤል ለአርብቶ አደሩ የንጹሕ ውሃ አገልግሎት ለማቅረብ 1ሺ 654 የተለያዩ የውሃ ተቋማት እንዲቋቋሙ መደረጉን ገልጸዋል ።
የትምህርት ተደራሽነቱን ለማሳደግ በአራቱም ክልሎች በአምስት ዓመታት ውስጥ 645 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት እየሠጡ እንደሚገኝ የጠቀሱት አቶ ሳሙኤል የትምህርት ሽፋን በጋምቤላ 97 በመቶ ፣ በቤኒሻንጉል 94 ፣ በአፋር 64 እና በ ሶማሌ 67 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል ።
በአምስት ዓመታት ብቻ በተጨማሪ በአራቱም ታዳጊ ክልሎች 482 የሰው ጤና ኬላ፣ 414 የሚጠጉ የእንስሳት ጤና ኬላዎችና 278 የአርብቶ አደር ማሠልጠኛዎች ተገንብተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሠጡ መሆናቸውን አቶ ሳሙኤል አስገንዝበዋል ።
በአርብቶ አደሩ በሚኖርባቸው አካባቢዎች የድርቅ ተጋላጭነትን ለመቀነስ በማሳብ የመንደር በአራቱም ክልሎች ውሃማ በሆኑ አካባቢዎች የመንደር ማሰባሰቡ ማካሄዱን የሚገልጹት አቶ ሳሙኤል የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራሙ የድርቅ ተጋለጭነት እንዲቀንስ ማድረጉን አብራርተዋል ።
በአገሪቱ ተመጣጣኝ ልማትን ለማረጋጋጥ ተግባራዊ በሆነው የአርብቶ አደር መንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም እስካሁን የፌደራልና የክልል መንግሥታት በመደቡት 7 ቢሊዮን ብር ወጪ እየተከናወነ ይገኛል ።