“በሕገወጦች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ  ሁሉም የጸጥታ ሃይሎች ታዘዋል” ጠ/ሚኒስትር ሃይለማሪያም

የአገሪቱንየተረጋጋ ህይወትና ሰላም ለማደፍረስና ልማቷን ለማደናቀፍ ዓልመው በሕገወጥ መንገድ ሁከትና ብጥብጥ በሚፈጥሩ ግለሰቦች ላይ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወስዱ ሁሉንም የጸጥታ ሃይሎች ትዕዛዝ መሰጠቱን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ አስታወቁ። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት መንግስት የህግ የበላይነትን በማስከበርና ሰላምን በማስፈን ረገድ ያለውን ሚና ለድርድርና ለጥያቄ እንደማያቀርብ ጠቅሰው በማንኛውም መንገድ ለሰዎች ህይወት ማለፍና ንብረት መውደም የሚደረጉ ሕገወጥ ሰልፎችም ሆነ ግጭቶችን እንደማይፈቅድ አስታውቀዋል።

ሰላምን የማስከበር ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስተሩ  መንግስት ሕቡእ አጀንዳ ይዘው አገሪቱን ለማተራመስ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በብቃት በመግታት የህዝቡን ሰላምና ደህንነት በተገቢው መንገድ ያስጠብቃል ብለዋል።

አንዳንድ ጽንፈኛ የዲያስፖራ አካላት  የኢትዮጵያን ልማት ለማደናቀፍ ሰላሟን ማደፍረስ ከሚፈልጉ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መቀበላቸውንና ከፊሉን ተጠቅመው ከፊሉን ለዚህ ብጥብጥ እያዋሉት መሆናቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒትሩ በሕገወጥ መንገድ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ማንኛውም አስፈላጊ እርምጃ እንዲወሰደ ሁሉንም የአገሪቱን የጸጥታ ሃይሎች ማዘዛቸውን ገልጸዋል። 

ይህንን አገር የማተራመስና ህዝብን የማበጣበጥ ተግባር መንግስት በዝምታ አይመለከተውም ሕብረተሰቡም ልጆቹ የሌሎች አገራቸውን በገንዘብ የሸጡ ጥቅመኞች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ መምከር ይኖርበታል ብለዋል።

መንግስት የወጣቱን ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ተቀርጸው የነበሩ ፓኬጆችን በከፍተኛ አመራር ደረጃ ታይተው አብዛኛውን ወጣት ተጣሚ ማድረግ በሚያስችል መንገድ  መዘጋጀታቸውንና ከወጣቱ ጋር በሚደረገው ውይይት ጸድቀው በወጣቱ ባለቤትነት ወደስራ እንደሚገባ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም  ወጣቱ ለሌሎች መጠቀሚያ ከመሆን እንዲታቀብም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።