የወልቃይት የማንነት ጉዳይ  ክልሎች ሲዋቀሩ አብሮ የተወሰነ ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ

የወልቃይት የማንነት ጉዳይ ክልሎች ሲዋቀሩ አብሮ የተወሰነ ጉዳይ በመሆኑ በወቅቱ የህዝብን ማንነት መሰረት አድርጎ  በተፈጸመው አከላለል   ወልቃይት በትግራይ ውስጥ መካሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ተናግረዋል።  

ጠቅላይ ሚኒስተሩ በዛሬው እለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሰመሩበት አገሪቱ የሚትከተለው የፌዴራል ስርዓት የህዝብን ማንነት መሰረት ያደረገ በመሆኑ በወልቃይት የሚነሳ ጥያቄ ካለ ለትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ቀርቦ ሕገመንግስታዊ ስርዓቱን ተከትሎ ሊመለስ ይገባል ብለዋል።

 

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ  ብሄራዊ  ክልሉ ለሚቀርብለት  ጥያቄ  ሕጉ በሚፈቅደው የጊዜ ገደብ  መልስ መስጠት ካልቻለ ጥያቄው ደረጃውን ጠብቆ  ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መቅረብና መፍትሄ ማግኘት ።

 

እሳከሁን ድረስ ሕገመንግስቱ በሚፈቅደው የአሰራር ስርዓት መሰረት  ለትግራይ ክልል ብሄራዊ መንግስት የቀረበ  ጥያቄ እንደሌለ ክልሉ ያረጋገጠ ሲሆን ጉዳይ ሲቀርብለት አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣል ብለዋል።

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም  በአማራና በትግራይ ክልሎች ያለው የድንበር ማካለል ችግር በሁለቱም ወገን ያለው ህዝብ ድንበሩን እንዲካለልለት ያቀረበው  ጥያቄ በወቅቱ አለመፈታቱ የሁለቱም ክልል ከፍተኛ አመራሮች ችግር እንደሆነ የኢህአዴግ ምክር ቤት መገምገሙን ተናግረዋል።

 

የአማራና የትግራይ ህዝቦች በማይበጠስ ገመድ የተሳሰሩ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስተር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ችግሩ ሁለቱ ህዝቦች በጋራ እንዲፈቱት ሰጥተናቸው ቢሆን ኑሮ በወቅቱ በቀላሉ መፍታት ይችሉ  ነበር ብለዋል።  

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም ሁለቱም ከፍተኛ አመራሮች የተፈጠረው ችግር በራሳቸው ክፍተት የመጣ መሆኑን በመገንዘብ ግለሂስ ማድረጋቸውን ጠቁመው ችግሩን በአፋጣኝ ለመፍታት በምክር ቤቱ አቅጣጫ መሰጠቱንና ሁለቱም ወገኖች  ችገሩን በቅርቡ ለመፍታት መስማማታቸው ገልጸዋል።