ወጣቱ ጥያቄዎችና ልዩነቶችን ህጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት እንዳለበት ገለጸ

ወጣቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱ ጥያቄዎችና ልዩነቶችን  ህጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ የመፍታት ባህል ማዳበር እንዳለበት የፌደራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ካሳ ተክለብርሃን  ገለፁ፡፡

በአራተኛ አገር አቀፍ የወጣቶች ጉባኤ ላይ በፌዴራሊዝም ስርዓት ላይ ከወጣቶች ጋር ውይይት በተካሄደበት ወቅት ሚንስትሩ ሰላም፣ የህግ የበላይነትና ህገመንግስት በማክበር የጸረ ድህነት ትግሉን ማስቀጠል ይገባል፡፡

በውይይቱም ወጣቶቹ አሁን ስላለው ወቅታዊ ሁኔታና የመልካም አስተዳደር ችግር ናቸው ያላቸውን በርካታ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

ከሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ተያያዞ በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አሉ፤ እነዚህን ጥያቄዎች  በሰላማዊ መንገድ በመታገል የተጀመረውን ልማት ማሳካት ይቻላል ብለዋል፡፡ ይህ ካሆነ ግን አንድ ትውልድ የማይፈታው ድህነት ውስጥ እየወረድን እንሄዳለን ነው ያሉት አቶ ካሳ፡፡

ወጣቶች በደንብ መገንዘብ ያለባቸው፣ በኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እየተመዘገበ ነው፤ ይህ ደግሞ በህብረተሰብ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስልጣን በመመስረት የመጣ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

 

“ኢህዴአግ በተለያዩ መድረኮች ላይ ችግሬ የመልካም አስተዳደር ነው ይላል ይህንን በዘላቂነት ለመፍታት ግን እያደረገ ያለው ምላሽ የዘገየ ነው ይህ ከምን መጣ?“” የሚሉ  ጥያቄዎች ከወጣቶች ቀርበዋል፡፡

 

መንግስት ዘላቂ መፍትሄ ያመጣሉ ብሎ በዘረጋቸው አሰራሮች አማካኘነት ችግሮችን በብቃት ለመፍታት የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች  የአክራሪነት አመለካከት ያላቸው ሃይሎችም ህዝቡን በተለይም ወጣቱን በተሳሰተ መንገድ ለመጠቀም እየተንቀሳሰቀሱ መሆናቸውን ያሳየ እንደሆነም አቶ ካሣ ገልጸዋል፡፡

ህጋዊ ጥያቄዎችን መጠየቅና ሀገር ማፈራረስ ማለት የተለያዩ ናቸው ያሉት አቶ ካሳ አሁን ያሉ ግርግሮቹ ስንመለከታቸው ለወጣቱ የስራ ዕድል፣ ኑሮ ለመሻሻል ከማሰብ ይልቅ የኢንቨስትመንት ተቋማትን ማፍረስ አገሪቱ ወደ ብጥብጥና ለመውሰድ የመፈለግ ዝንባሌ ያላቸው ሃይሎች እንዳሉ የሚያሳይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ወጣቱም እያደገ የመጣውን የዴሞክራሲ መብቱን ተጠቅሞ ችግሮች በውይይት በመፍታት ሀገርን በዘላቂነት ከድህነት ለማወጣት በሚደረገው ጥረት ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል፡፡