መንግሥት የወጣቱን ችግር ለመፍታት ሰፋፊ መድረኮች ማዘጋጀት አለበት – የአገሪቱ ወጣቶች

መንግሥት  የወጣቱ  የህብረተሰብ  ክፍል በህይወቱ ውስጥ  የሚያጋጥመውን ችግር መፍታት  እንዲችል  የተለያዩ ሰፋፊ መድረኮችን በማመቻቸት ከወጣቱ ጋር ውይይቶች ማካሄድ እንደሚጠበቅበት  በተለያዩ  የአገሪቱ  ክፍሎች የሚኖሩ ወጣቶች ገለጹ ።

በ4ኛው አገር አቀፍ የወጣቶች ተሳትፎና ንቅናቄ መድረክ ላይ የተሳተፉ  ወጣቶች ለዋኢማ አስተያያታቸውን በሠጡት ወቅት እንደገለጹት በአገር ደረጃ ወጣቱ በፖለቲካዊ ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚ ዘርፎች የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመፍታት  መንግሥትና  ወጣቱን  የሚያገናኙ መድረኮች የማማቻቸት ሁኔታ  መጠናከር አለበት ብለዋል ።

የወላይታ ነዋሪ የሆነው ወጣት ሙሴ አንጀሎ እንደሚናገረው እሱ በሚኖርበት አካባቢ ወጣቶች  ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሠማሩ ቢሆንም ወጣቶች በሥራ ሂደት  የሚያጋጥማቸው ችግሮች ለመፍታት ከአስተዳደር  አካላት ጋር ትኩረት ተሠጥቶት  ውይይት  ማካሄድ  ያስፈልጋል ብሏል ።

እንደ ሙሴ ገለጻ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር በአገር አቀፍ ደረጃ  ወጣቱንና  የወጣቱን ተወካይ  ያወያያዩት ከአምስት ዓመት በኋላ መሆኑ  በመንግሥት የትኩረት  ማነሰ ሁኔታ  እንደሚታይ ተናግሮ   ጠቅላይ ሚንስትሩ  በኮንፈረንሱ ውይይት በመዘግየቱ ይቅርታ በመጠየቅ ለወደፊቱ  በአጭር ጊዜ  ወጣቱን እንደሚያወያያ ቃል በመግባታቸው መደሰቱን ገልጿል ።

ሌላዋ  የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ወጣት ፍሬህይወት በበኩሏ ወጣቶች የራሳቸውን ሥራ ፈጠረው እንዲንቀሳቀሱና ስኬታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ከሥልጠናና ከገንዘብ ብድር ጀምሮ በአግባቡ ተሟልተው ሊመቻቹ የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉ ጠቁማ መንግሥት  የወጣቶች ድጋፍ  በተመለከተ ያለበትን  ውስንነትን ሊቀርፍ ይገባል ብላለች ።       

የድሬዳዋ  ነዋሪው ወጣት ኤልያስ ሬያሌ እንደሚለው የወጣት  አደረጃጃቶች  ለወጣቱ የማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፈታት ይበልጥ ትግል ማድረግ እንደሚገባቸው  በመጠቀስ ወጣቱ ከተናጠል ይልቅ  በአንድነት መንቀሳቀሱ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያግዝ ገልጿል ።

በአማራ ክልል ነዋሪ የሆነችው  ወጣት ሄለን ብርሃኑ እንደገለጸችው አሁን በጠቅላይ ሚንስትሩ  የተጀመረው  ወጣቶችን የማወያየት እርምጃን አድንቃ በቀጣይ ግን እስከ ታችኛው  የአስተዳደር አካላት ድረስ በርካታ  ውይይቶች በተለያዩ  አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከወጣቱ  ጋር በማድረግ ችግሮች መንቀስ እንደሚቻል ታምናለች ።