በአማራ ክልል ግጭት ተፈጥሮባቸው የነበሩ አካባቢዎች በመረጋጋት ላይ መሆናቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ባህር ዳርን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ ግጭቶች መንግስትና ህዝቡ ባደረጉት ጥረት መረጋጋት እየሰፈነ መሆኑን ነው ፅህፈት ቤቱ ለዋልታ የገለፀው፡፡
በክልሉ ተከስተው በነበሩት ግጭቶች የመንግስትና የህዝብ ሀብት በመውደሙ መንግስት የተጠናከረ የፀጥታ ኃይል በመመደብ ግጭቶች እንዲቆሙ መደረጉን የፅህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡
የህዝብ ጥያቄ ያልሆኑ ህይወት የማጥፋና ሀብት የማውደም ህገ ወጥ ድርጊትቶችን በሚፈፅሙ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ ህዝቡም ፅንፈኛና ህገ ወጦችን እየጠቆመ ለህግ እንዲቀርቡ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
መሳሪያን በመጠቀም የማጥቃት እንቅስቃሴ በመስተዋሉ መንግስት ለፀጥታ ኃይሉ ልዩ ትኩረት በመስጠቱ የፀጥታ ኃይሉ መዋቅር በቂ ዝግጅት ማድረጉን አቶ ንጉሡ አስገንዝበዋል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ አለመረጋጋቶችም ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው እንዲመለሱ ከህዝቡ ጋር በመሆን ሰፊ የማረጋጋት ሥራ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ ህዝባዊ መድረኮችን በማዘጋጀት የማወያየቱ ጥረትም ለዚህ ጉልህ አስተዋፅዖ ማበርከቱን አስረድተዋል፡፡
በንግድ፣ በተለያዩ አገልግሎቶችና የትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማትም በሚፈለገው መጠን ባይሆንም የቀደመውን ዓይነት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አቶ ንጉሡ ተናግረዋል፡፡ ሌሎቹም ተቋማት ከስጋት ተላቀው በተሰማሩበት ዘርፍ አገልግሎቱን እንዲሰጡ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡ ከስጋት ተላቆ ሠላማዊ እንቅስቃሴውን እንዲጀምር ሰፊ ውይይት እየተደረገ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝም ህዝቡ አካባቢውን እንዲጠብቅና ለሠላም ዘብ እንዲቆም እየተሰራ ነው ይላሉ፡፡
ባለፈው ሰኞና ማክሰኞ ፀረ ሰላም ኃይሎች በፈጠሩት ሁከትና ግርግር በመራዊ፣ መሸንቲና ወንጀጣ አካባቢ ባሉ የአበባና የአትክልት እርሻ ልማት ኘሮጀክቶች ላይ ጉዳት መድሩን ከክልሉ የተገኙት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በዚህም ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መግለፁ ይታወሳል፡፡