በሠላምና ልማት ዙሪያ የሚካሄዱት ህዝባዊ መድረኮች ተጠናክረው ቀጥለዋል

ሠላምን በማስፈንና ልማትን ለማጠናከር በሚያስችሉ ነጥቦች ዙሪያ የተጀመሩት ህዝባዊ መድረኮች ተጠናክረው መቀጠላቸው ተመለከተ፡፡

ዋልታ በተለያዩ ክልሎች እየተካሄዱ የሚገኙ ህዝባዊ መድረኮችን በማስመልከት ባጠናቀረው መረጃ ህብረተሰቡን ያሳተፉ የውይይት መድረኮች በስፋት እየተካሄዱ ነው፡፡

በአማራ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች የተነሳውን ግጭት ተከትሎ በሰው ህይወትና አካል ላይ የደረሰውን ጉዳትና የንብረት ውድመት ተከትሎ ከህብረተሰቡ ጋር ሰፊ ውይይት መጀመሩን የክልሉ የኮሙኒኬሽን ፅህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ገልጸዋል፡፡

በህዝባዊ መድረኮቹ ህዝቡ ህገ ወጥ ድርጊቶችን ከማውገዝ በተጨማሪ ለሠላምና ልማት የሚጠበቅበትን ለመወጣት ቃል መግባቱን ዳይሬክተሩ ይገልጻሉ፡፡

ሠላምን ለማወክ የሚንቀሳቀሱ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ማሳሰቡን ነው ያስገነዘቡት ፡፡

ከመልካም አስተዳደር እጦት ጋር በተያያዘ ከህዝብ ለሚነሱ ቅሬታዎችም አፋጣኝና ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጥ አቶ ንጉሡ ጠቁመዋል፡፡

በጋምቤላ ክልል እየተካሄደ ያለው የውይይት መድረክም ህዝቡ ለሠላምና ልማት ቆርጦ መነሳቱን ያንፀባረቀ መሆኑ ነው የተገለፀው፡፡

የጋምቤላ ክልል ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኦኬሎ ኡማን እንዳስታወቁት ህዝቡ በህገ መንግስቱ የተረጋገጠለትን መብትና ነፃነት አስከብሮ ለመጓዝ በንቃት ይሳተፋል፡፡

እስከ ቀበሌ ድረስ የዘለቀው ህዝባዊ የውይይት መድረክ የሰላም አስፈላጊነት በስፋት የተወሳበት መሆኑን አቶ ኦኬሎ አስረድተዋል፡፡

የክልሉን ልማትና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወሳኝ የሆነውን ሠላም በአስተማማኝነት ለማስፈን ህዝቡ ዘብ እንደሚቆም አስረድተዋል ፡፡

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝባዊ መድረኮች ጥሩ ውጤት ማስገኘታቸውን ነው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አምባሳደር ምስጋናው አድማሱ የገለጹት ፡፡

በመድረኮቹ ህዝቡ መሻሻልና መጠናከር የሚገባቸውን ጉዳዮች በማንሳት የተሻለ ውጤት እንዲመጣ በሚመለከተው አካል ትኩረት እንዲሰጥ ማሳሰቡንም አስረድተዋል፡፡

በሠላምና ልማት ዙሪያ ያኮሩት ህዝባዊ መድረኮቹ በቀጣይም ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ታውቋል ፡፡