የኢህአዴግ የውስጥ ችግሮች ለተከሰቱት ሁከቶቹ መንስኤ ናቸው – አቶ ከበደ ጫኔ

የዴሞክራሲ ተቋማት አለመጠናከርና የኢህአዴግ የውስጥ ችግሮች በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ለተከሰቱት ሁከቶቹ መንስኤ መሆናቸውን የኢህአዴግ እና ብአዴን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ከበደ ጫኔ ገለጹ ።

አቶ ከበደ ጫኔ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ  በሰጡት ማብራሪያ በህዝብ ጥያቄ ተከልለው ሀገሪቱ ወደለየለት የእርስ በርስ ግጭት እንድትገባ የሚፈልጉ ሃይሎች እያራመዱት ያለ ተቀባይነት የሌለው አካሄድ ስለመታየቱም ጠቁመዋል።

ለተፈጠሩት ሁከቶች የህዝብን ጥያቄ በአፈጣኝ አለመመለስ፣ የመልካም አስተዳደር እጦት እና በቂ የስራ እድል ፈጠራ አለመኖር ከሚሉት ውጭ የሆኑ  ሌሎች ምክንያቶችንም አንስተዋል።

የመሪው ድርጅት ኢህአዴግ የውስጥ ዴሞክራሲ መሳሳትን ቀዳሚው ምክንያት ያደርጉታል።

የሚታገል፣ የተለየ ሀሳብ የሚያቀርብ ሰው በየመድረኩ እየተኮረኮመ ነው ያሉት አቶ ከበደ፤ ይህ የውስጥ ዴሞክራሲ አለመጠናከር የዴሞክራሲ ተቋማት በሚገባው ልክ እንዳይጠናከሩ አድርጓል ብለዋል።

አስፈፃሚውን የመቆጣጠር ስልጣን ያላቸው ከወረዳ እስከ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሉት የህዝብ እንደራሴዎችም ሊቆጣጠሩት በሚገባው አካል ተፅእኖ ስር የሚወድቁበት ጊዜ መኖሩን አመልክተዋል ።

ስልጣንን የራስ መገለገያ የማደረግ አባዜም ከሌሎቹ መንስኤዎች ጋር ተዳምሮ የህዝብ ፍላጎትን ተከትሎ ምላሽ ያለመስጠትን እያስከተለ ነው የሚሉት።

በዚህ ምክንያት በህዝብ ልብ ወስጥ ያደረ ቅራኔ ወቅታዊ ስበብን ተከትሎ ገነፈለ ያሉት አቶ ከበደ፤ ለአማራ ክልል ሰሞነኛ ሁከት ወቅታዊ መንስኤ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ የአማራ እና ትግራይ ክልል አንድ የወሰን ማካለል ጥያቄን በቀላሉ መፍታት አለመቻል ነው ብለዋል።

“አማራ ክልል ላይ የተፈጠረው ችግር አንዱ ፀገዴ እና ጠገዴ የሚባለው ወረዳ ከ1984 በፊት 28 ቀበሌ ይዞ አንድ ወረዳ ነበር የነበረው፤ ቋንቋን መሰረት አድርጎም ወደ ትግራይ መካለል እንፈልጋለን ያሉ 16 ቀበሌዎች ወደ ትግራይ፣ 12 ቀበሌዎች ደግሞ ወደ አማራ እንካለል በማለታቸው ወደ አማራ ክልል እንዲካለሉ ተደርጓል።” ነው ያሉት የኢህአዴግ ፅህፈት ቤት ሃላፊው ።

ከዚህ ማካለል በኋላ ከ28ቱ ቀበሌዎች በአንዱ ቀበሌ ብቻ ያልተቋጨ ወሰን ማካለል እንደነበር ጠቁመዋል ።

የወልቃይት ጉዳይም፤ሁከት እና ግጭትን የሚያስከትል ጉዳይ አልነበረም ባይ ናቸው።

የወልቃይት ማንነት ጥያቄ ማቅረብ የሚፈልግ አካልም ጥያቄውን በህጉ መሰረት ለትግራይ ክልል መንግስት ማቅረብ ይችላል፤በተቀመጠው ጊዜ ምላሽ ካላገኘም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረብ መብት መሆኑንም አቶ ከበደ አንስተዋል።

ነገር ግን ይላሉ አቶ ከበደ ህዝቡ ጥያቄዎቹ በህግ እና ስርኣት እንዲመለሱ የሚፈልገውን ያህል ጉዳዮቹን የተከተለ ሀገራዊ ብጥብጥ እና የህዝብ ለህዝብ ፍጅትን እንዲያስከትሉ የሚፈልጉ ሃይሎች መኖራቸውን አመልክተዋል ።

መንግስት እርስ በእርስ የሚጠፋፉ የሚላቸው ሃይሎች ትብብር ጥፋት የሆነ ስብከትን መጀመራቸውንም ገልጸዋል ።

በእርግጥ ይህንን የጥፋት አዋጅ ኢትዮጵያውያን አልተቀበሉትም ያሉት አቶ ከበደ ፤የሰሜን ጎንደር አብዛኛው አማራ ለትግራይ እህት እና ወንደሞቹ ያሳየው አጋርነት የሁለቱ ህዝቦች የማይበጠስ ትስስር ማረጋገጫም መሆኑን አስረድተዋል ።

ኢህአዴግም ያሉትን ችግሮች በአዲሱ አመት ለመፍታት ውሳኔ አስቀምጦ ወደ ተግባር ገብቷል ብለዋል፡፡

የኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት ሃላፊው  በጋራ መስዋዕትነት የጋራ አዲስ ሀገር ለገነቡት ኢትዮጵያውያን የአዲስ አመት የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላልፈዋል-(ኤፍ.ቢ.ሲ)።