የህዝብ አገልጋይነትን የተላበሰ የፐብሊክ ሰርቪስ ሥርዓትን እውን ለማድረግ መንግስት በትኩረት ይሠራል

ቁርጠኛ የህዝብ አገልጋይነትን የተላበሰ የፐብሊክ ሰርቪስ ሥርዓትን እውን ለማድረግ መንግስት በአዲሱ ዓመት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደርና ሪፎርም ክላስተር አስተባባሪና የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስትሯ ወይዘሮ አስቴር ማሞ ተናገሩ።

ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት በቀሩት 2008 ዓ.ም የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሠጣጥ ችግር የህዝብና የመንግስት መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።

መንግስትም ቀድሞውንም ልዩ ትኩረት ያሻቸዋል፤ ለብልሹ አሠራር ተጋላጭ ናቸው ባላቸው ተቋማት አመራሮችና ፈፃሚዎች ላይ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ሞክሯል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አሰተዳደርና ሪፎርም ክላስተር አስተባባሪና የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስትሯ ወይዘሮ አስቴር ማሞ፥ መልካም አስተዳደር ለማስፈን በተደረገ እንቅስቃሴ የተሻለ ውጤት ቢታይም ማዕቀፉን በተሟላ ሁኔታ በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ትኩረትን የሚጠይቅ ሥራ አለ ብለዋል።

በ2008 ዓ.ም መንግስት በህዝቡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በሚገባ በማወቅና በመለየት የተጠያቂነት ስርዓትን ለመዘርጋት የጀመረው ጥረት ብዙ ይቀረዋልም ነው ያሉት።

እነዚህ ጅምር ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም መንግስት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የተጠያቂነት ስርዓቱ በብልሹ አሰራርና በመጥፎ ስነ ምግባር የተዘፈቁ አመራሮችና ፈፃሚዎችን፥ በተመደቡበት ስራ ላይ ባስመዘገቡት ውጤት መሰረት በመመዘንና ተጠያቂ በማድረግ በማድረግ እርምጃው እንደሚደረግም ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ የተመደቡበትን ስራ በውጤታማነት ያለመፈፀም አንዱና ዋነኛው የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭና የብልሹ አሰራሮች በር መክፈቻ በመሆኑ ነው ብለዋል።

ይህን ውጤት መሰረት በማድረግ እርምጃ ከመውሰዱ ጎን ለጎን በስራቸው ግንባር ቀደም በመሆን የላቀ ውጤት የሚያስመዘግቡ ሰራተኞችን በቀጣይ ዓመት ለማበራከት ትኩረት መሰጠቱንም ነው ያነሱት።

ቀድሞ መንግስት የጀመራቸው የትራንስፖርትና የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ፓኬጆችን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲሆኑ ማስቻል የዚህ እቅድ አካል እንደሆነም አስረድተዋል።

ህዝቡም መንግስት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በሚወስዳቸው እርምጃዎችና ማሻሻያዎች የራሱን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።( ኤፍቢሲ)