ደኢህዴን የ15 አመታት የተሀድሶ ጉዞውን በመገምገም በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄውን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገለፀ

የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን/ ያለፉት 15 አመታት የተሀድሶ ጉዞውን በመገምገም በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄውን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገለፀ፡፡

ባለፈው ሳምንት የኢህአዴግ ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የተጀመረው ይህ ንቅናቄ የክልሉን ህዝብ ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አንፃር ታሪካዊና በጥልቀት የመታደስ ተጨባጭ ውጤት የሚያረጋግጥ ይሆናል ሲል ነው የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ የገለፀው፡፡

ማዕከላዊ ኮሚቴው በቆይታው ባለፉት 15 አመታት ከተሀድሶ በኋላ በክልሉ የተመዘገቡ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ተግባራት አፈፃፀሞችን በዝርዝር መገምገም ጀምሯል፡፡

 

በቆይታውም በገጠርና በከተማ ድህነትን በመቅረፍና የህዝቡን ኑሮ በመለወጥ ረገድ የነበረውን አፈፃፀም ማዕከላዊ ኮሚቴው በተገቢው እንደሚፈትሽ ነው የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቲ ጽህፈት ቤት የገለፀው፡፡

 

ደኢህዴን /ኢህአዴግ/ በክልሉ የሚገኘውን መላ ህዝብ በማንቀሣቀስ የተመዘገቡ ውጤቶችንና በሂደቱም የተስተዋሉ ጉድለቶችን ከመቼውም ጊዜ በተለየ መንገድ በጥልቀት እንደሚያይ የገለፀው ጽህፈት ቤቱ በተለይም ባለፈው አመት በድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ተገምግሞ አቅጣጫ የተቀመጠበትን የልማታዊ መልካም አስተዳደር ተግባራት አፈፃፀምን በጥልቀት እንደሚገመግም አስታውቋል፡፡

 

በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ረገድ ክልላዊ አንድነትን በማጠናከርና የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረውና የክልሉ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ በኩል ጐልብተው የሚቀጥሉበት ሁኔታ ላይም የሚመክር ይሆናል፡፡

 

ማዕከላዊ ኮሚቴው የክልሉ ወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃማነት ላይ የሚስተዋሉትን ድከመቶች በስፋት የሚፈትሽ ሲሆን በገጠርና በከተማ የሚገኘውን የመላው ህዝብ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተደደር ጥያቄዎች በዝርዝር ታይተውና የህዝቡን እርካታ ሊፈጥሩ በሚችል መንገድ ተግባራዊ የሚደረጉበት ሁኔታ ላይ በስፋት በመምከር ውሣኔ እንደሚያስተላልፍም ይጠበቃል፡፡

 

 

ይህ ታሪካዊና በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ደረጃ በደረጃ እስከ ህዝቡ እንደሚወርድና በሂደቱም የክልሉን ህዝብ ያሳተፈ ተጨባጭ የመታደስ ውጤት እንደሚመዘገብ ይጠበቃል በማለት የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡ (EBC)