በኦታዋ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ14 ሺ የካናዳ ዶላር በላይ ተሰበሰበ

በካናዳ ኦታዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ 14 ሺ አምስት መቶ የካናዳ ዶላር ድጋፍ አደረጉ።

ገንዘቡ የተሰበሰበው መጪውን አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ በተካሄደ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ነው።

በዝግጅቱ ላይ በኦታዋ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተቀዳሚ ጉዳይ ፈጻሚ አቶ ነቢያት ጌታቸው ኢትዮጵያን ከድህነትና ከኋላቀርነት ለማላቀቅ የግድቡን ስራ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ዳያስፖራውም ሲያደርገው የቆየውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኦታዋ የህዳሴው ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኪዳኔ ገብረማርያም በበኩላቸው በከተማዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የግድቡ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ ያልተቋረጠ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

በቀጣይም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቱ ላይ የኦታዋ ከተማ ከንቲባ ተወካይ፣ የአፍሪካ- ካናዳ ማህበር ፕሬዝዳንትና ጥሪ የተደረገላቸው የኢትዮጵያ ወዳጆች ተገኝተው ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አጋርነታቸውን መግለጻቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ገልጿል።(ኢቢሲ)