አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በብሩህ ተስፋ የተሞላ ነው -መንግስት ኮሙኒኬሽን

ጽህፈት ቤቱ ባወጣው መግለጫ አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በብሩህ ተስፋ የተሞላ መሆኑን አመልክቷል ፡፡

ህዝብ ያጣጣመው ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ በብልሹ አሰራር ምክንያት እንዲበላሽ አለመፈለጉን በግልጽ አሳይቷል ብሏል ፡፡

ጉዳዩን ወደ ራሳቸው የጥፋት አጀንዳ ለመቀየር የፈለጉ አካላትን በማግለልም በተዘጋጁለት የውይይት መድረኮች ጭምር ጥያቄውን በግልጽ እያቀረበ እንደሚገኝ አስታውቋል ፡፡

መንግስትም ብዙዎች የተሰዉለት ህዝባዊና አገራዊ ራዕይ በጥቂት ጥገኞች ምክንያት እንዳይመክን ታሪካዊ ውሳኔ በቁርጠኝነት ማሳለፉን አረጋግጧል ፡፡

መንግስት ከህዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት ከፍተኛ ርብርብ የሚያደርግበት ዓመት እንደሚሆንም ገልጿል ፡፡

በተለይም በወጣቱ የተነሱ ጥያቄዎችን መመለስ የሚችሉ ስር ነቀል ማሻሻያዎች የሚደረጉበት መሆኑንም አመልክቷል።

የተጀመረው የዕድገት ግስጋሴን የማቀዝቀዝ አቅም ያላቸው ስሜቶች የሚቀየሩበት፣ ዲሞክራያዊ ስርዓት ግንባታችን የሚጎለብትበት፣ ኢኮኖሚያችንን ለማሸጋገር አቅም ያለው የሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ በሙሉ አቅም የሚፈፀምበት ጊዜ እንደሚሆን አብራርቷል መግለጫው ፡፡

 ባጠናቀቅነው በጀት ዓመት ለዚህ የህዝብና የመንግስት ፍላጎት እንቅፋት የሚሆኑ ተግባራት ቅሬታና ተቃውሞ እስከ ማስነሳት መድረሳቸውን አመልክቷል ፡፡ 

ከዚህ በመነሳትም መንግስት መንስኤዎችን በጥልቀት ለመፈተሸ ተገዷል ያለው መግለጫው ፤ እየተመዘገበ ያለው ፈጣን ዕድገት ሁሉንም ዜጎች በእኩል እንዳይጠቅም እንቅፋት የፈጠረው “መንግስታዊ ስልጣንን ለግል ጥቅም የማዋል ዝንባሌ መፈጠሩ” መሆኑንም መንግስት መረዳቱን አንስቷል፡፡

መንግስታዊ መዋቅሩን በጥልቀት ገምግሞ ስር ነቀል በሆነ ደረጃ ለማሻሻልም ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቋል ፡፡

የሀገራችንን የቀደመ ታላቅነት ለመመለስ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብዙ ዋጋ ያለው መግለጫው፤ በዚህም ለህዳሴ ጉዞ መሰረት የሚሆን በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነትን መገንባቱን ጠቁሟል ፡፡

በኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነታቸው ላለፉት ዓመታት ባደረጉት የተቀናጀ ርብርብ ተከታታይ ዕድገት ማስመዝገባቸውን ጠቅሷል ፡፡

በተለይም መንግስታዊ ስልጣንን ለህዝብ ጥቅም ብቻ ለማዋል አቅደው በመስራታቸው መላ ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረገ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ችለዋል ብሏል ፡፡

የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ አሁን አገራችን ከደረሰችበትና ህዝባችን ከሚፈልገው ደረጃ ጋር መጣጣም እንደሚኖርበት አስገንዝቧል ፡፡

በዚህም ሀገራችን በቀጠናው በአህጉራዊና በአለም አቀፍ መድረኮች ከፍ ብላ መደመጥ ጀምራለች ሲል አመልክቷል ፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ይህ አንፀባራቂ ጉዞ ከዚህም በተሻለ ፍጥነት እንዲቀጥል ካሳለፍነው በጀት ዓመት ብዙ ተምረዋል ነው ያለው ፡፡

በትምህርት፣ በጤና እና በመሰረት ልማት መስፋፋት ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ ያደገውን የህዝባችንን የተጠቃሚነት ፍላጎት የሚያረካ መንግስታዊ አስተዳደር መስፈን ይጠበቅበታልም ብሏል ፡፡

የህዝብ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተቀረፁ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና አሰራሮች በትክክል መተግበራቸው መረጋገጥ እንደሚነርበትም ጠቁሟል ፡፡

የኢፌዴሪ መንግስት ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች “እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ” እያለ፣ የዕድገት ተስፋችንን ብሩህ ለሚያደርጉ እነኚህ የህዝብና የመንግስት ውሳኔዎች ተፈጻሚነት፡ በአዲሱ በጀት ዓመት፡ በአዲስ መንፈስ  ከመንግስት ጎን መቆማቸውን እንዲቀጥሉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ አቅርቧል ሲል ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ፡፡