ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ለሠላም መስፈን ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ገለጹ

ሠላምን ለማስፈን ሁሉም ባለድርሻ አካል በመሆን ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ የተለያዩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ፡፡

በአገር ውስጥ ለሚደረግ ልማትና ማንኛውም እንቅስቃሴ ሠላም ዋናው መሰረት በመሆኑ ሁሉም ለሠላም ዘብ መቆም እንደሚገባው ለዋልታ አስተያየታቸውን የሰጡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስረድተዋል፡፡

ሠላምን ማስፈንና መጠበቅ የአንድ አካል ብቻ ባለመሆኑ ሁሉም የበኩሉን መወጣት ይኖርበታልም ብለዋል ፡፡

የቅንጅት ለአንድነትና ዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ አየለ ጫሚሶ ያለ ሠላም ልማትና ዕድገትን ማለም እንደማይታሰብ ያስገነዝባሉ፡፡

ስለሆነም ሠላምን ለማስፈንና መረጋጋት እንዲኖር መስራት ይገባል ብለዋል ፡፡

ወጣቱ በስሜት ተገፋፍቶ ወደ ሁከትና ብጥብጥ እንዳያመራ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ ሠላም ወዳድና የሠላምን ጥቅም ከማንም በላይ የሚያውቅ ነው›› የሚሉት ደግሞ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ሊቀ መንበር አቶ ትግስቱ አወሉ ናቸው፡፡

የሚፈለገውን ለውጥና ዕድገት ለማምጣት ሠላም ቀዳሚው ጉዳይ መሆኑን አቶ ትግስቱ ጠቅሰዋል፡፡

አክለውም አስተሳሰብን በማስፋት የሠላምን አስፈላጊነት ለትውልዱ ማስተማር ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡

ሠላምን ለማወክ የሚንቀሳቀሱ አካላት ከድርጊታቸው መታቀብ ይኖርባቸዋል ሲሉም አስገንዘበዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ፍትህና ዴሞክራሲ ኃይሎች ግንባር (ኢፍዴኃግ) ሊቀ መንበር አቶ ገረሱ ገሣ ሠላምን መጠበቅ የሁሉም ግዴታ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

ምላሽ የሚያሻቸው ጥያቄዎች ሲኖሩም በሠላማዊ መንገድ ማቅረቡ ውጤቱ የተሻለ ይሆናል ባይ ናቸው ፡፡

ጥያቄ የቀረበለት አካልም አፋጣኝና ተገቢ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባ ያመለከቱት አቶ ገረሱ፤ በሠላማዊ መንገድ የመወያየትና የመመካከር ባህልን ሁሉም ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል፡፡

ሁሉም አቅሙ በፈቀደ መጠን ሠላምን ለማስጠበቅ መትጋት እንዳለበት የመላው ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ንቅናቄ(መኢብን) ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ መሳፍንት ሽፈራው ይገልፃሉ፡፡

ሁሉም የአካባቢውን ሠላምና ፀጥታ የመጠበቅና የማስከበር ኃላፊነት እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት፡፡

መንግስትም ሠላምን የማስከበር ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል ያሉት ፕረዚዳንቱ፤ ከህዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሾችን መስጠት፤ችግሮች እንዲፈቱና እንዲወገዱ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ፓርቲዎቹ ለሠላም መበረዝና መታወክ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን በመፈተሽ መፍትሔ ማበጀት እንደሚገባ ያመለክታሉ፡፡