የክልሉ የዞን፣ የልዩ ወረዳና የወረዳ አወቃቀር የአስተዳደር ቅልጥፍናን የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረገ ነው

በደቡብ ክልል የዞን፣ የልዩ ወረዳና የወረዳ አወቃቀር የአስተዳደር ቅልጥፍናን፣ አመቺነትና የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ታሳቢ በማድረግ የሚካሄድ መሆኑን የደቡብ ክልል የብሄረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ለማ ገዙሜ ተናገሩ።  

የኮንሶ ወረዳም በሰገን ህዝቦች ዞን እንዲካተት የተደረገው ይህንን ታሳቢ በማድረግ መሆኑን ነው አፈ ጉባኤው የገለጹት።

የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤትም በእንዲህ መልኩ ከ4 እስከ 16 ብሄረሰቦችን በአንድ የዞን አስተዳደር በማሰባሰብ የተሰሩ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስቻሉ ናቸው ብሏል።

የደቡብ ክልል በ14 ዞኖችና 4 ልዩ ወረዳዎች የአስተዳደር መዋቅሮችን ያቀፈ ነው።

ዞኖቹም ይሁኑ ልዩ ወረዳዎቹ ሲዋቀሩ የህግ መንግስቱን መርሆችን መሠረት በማድረግና የህዝቦችን ቀጥታ ተጠቃሚነትና የአሰተዳደር ቅልጥፍን ቀዳሚ በማድረግ ነው።

የክልሉ ብሄረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ለማ ገዙሜ፥ የክልሉ 56 ብሄረሰቦች ይህን ታሳቢ በማድረግ በዞን እንዲዋቀሩ መደረጉን ገልፀዋል።

ህዝቡ በምን ዓይነት መንገድ የአስተዳደር ደረጃ ቢዋቅር የላቀ ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል የሚለው በጥናት እንዲመለስ እንደሚደረግም አንስተዋል።

የአስተዳደር መዋቁሩ ለጥቂት ግለሰቦች የሚፈጥረውን የስራ ዕድል ከማሰብ ይልቅ የህዝቡን አጠቃላይ ተጠቃሚነት ቀዳሚ ያደርጋል ያሉት ደግሞ የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን ናቸው።

ቀደም ሲል የኮንሶ፣ ደራሼ፣ ቡርጂና አማሮ የልዩ ወረዳ አወቃቀሮችን ለምን የሰገን ህዝቦች በሚል በዞን ለማዋቀር ክልሉ መርጠ በሚል ለሥራ  ኃላፊዎች  በተነሳው  ጥያቄ በተሠጠው ምላሽ ቀደም ብሎ ለህዝቡ ቀልጣፋ አስተዳደራዊ አገልግሎት በማቅረብ አስፈላጊውን የልማት ውጤት ለማምጣት ባለመቻሉ ነው ብለዋል ።

ለዚህም የክልሉ መንግስት ኮንሶን ጨምሮ በአራቱ ልዩ ወረዳዎች ልማት በሚፈለገው ደረጃ የህዝብ ተጠቃሚነት አለመምጣቱ በጥናት ማረጋገጡን ወይዘሮ ሂክማ አንስተዋል።

ልዩ ወረዳዎቹ ተጠሪነታቸው ለክልሉ ስለነበር የተወሰኑ አለመግባባቶች በተፈጠሩ ቁጥር ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ ጉዞ በማድረግ የክልሉ መቀመጫ ሀዋሳ ማቅናት ይጠይቃል።

ክልሉ ባደረገው ጥናትና በየደረጃ ከህዝቡ ጋር በተደረገው ውይይት አለመግባባቶችን ለመፍታት፣ ሃብትና የሰው ኃይል በጋራ በማሰባሰብ ለልማት ለማዋል ተመራጩ ዞን በአማካይ ቦታ ማቋቋም መፍትሄ ሆኖ መቅረቡን የክልሉ ብሄረሰብ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አውስተዋል።

በአራቱ ልዩ ወረዳዎች የተደረጉ ህዝባዊ ውይይቶችም ከልዩ ወረዳ ይልቅ አራቱ ልዩ ወረዳዎች በጋራ በዞን ደረጃ መዋቀር እንደሚሹ አረጋግጠዋል።

ይህም ከቀበሌ ጀምሮ ባሉ የአስተዳደር ምክር ቤቶች በይሁንታ መፅደቁን አስታውሰዋል።

ታዲያ የኮንሶ ህዝብ ጥያቄ ምንድን ነው? ኮንሶን በዞን ደረጃ እንዲዋቀር ለማድረግ በተደራጀው 23 አባላት ባሉት ቡድን አንዱ የሆኑ አቶ ገመቹ ገምሽ የህዝቡ ጥያቄ ይህ ነው ይላሉ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባወጣው የበጀት ድልድል ቀመር የደቡብ ክልል ይህን ቀመር ተከትሎ በክልሉ የሚገኙ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ይመድባል ነው ያሉት አቶ ለማ ገዙሜ።

የመልካም አሰተዳደር ጥያቄ ችግር ግን የክልሉ መንግስት ዞኑ በመቀናጀት ለመፍታት የተዘጋጁ ቢሆንም በኮንሶ አካባቢ ያለመረጋጋት መግጠሙ የተነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት እንቅፋት መሆኑንም አመላክተዋል።

አሁን የክልሉ መንግስት በአካባቢው ሰላም እና መረጋጋት እንዲመለስ ለማድረግ እየሰራ ነው።

የክልሉ መንግስት ዞን ለማዋቀር የህዝብ ቁጥርና የቆዳ ስፋት ዋነኛ መስፈርት አድርጎ አይወስንም፤ ይልቁንም ለህዝቡ ተጠቃሚነትና ለአስተዳደር ቅልጥፍና እና አመቺነት ያተኩራል።

አሁን በኮንሶ አካባቢ ያለውን አለመረጋጋት ሙሉ በሙሉ ወደ መረጋጋት በመመለስ የክልሉ መንግስት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅርፍ ይንቀሳቀሳል ብለዋል አቶ ለማ።( ኤፍቢሲ)