ብአዴን በጥልቀት የመታደስ የአመራር ንቅናቄውን በድልና በስኬት አጠናቀቀ

ብአዴን በጥልቀት የመታደስ የመጀመሪያውን ምዕራፍ የከፍተኛ አመራር ንቅናቄ መድረክ በድልና በስኬት አጠናቀቀ ።

ብአዴን "በጥልቀት በመታደስ ክልላዊና አገራዊ ህዳሴያችን እናፋጥን!" በሚል መሪ ቃል የከፍተኛ አመራር ኮንፈረንስ ከመስከረም 4 እስከ መስከረም 9 ድረስ በባህርዳር ከተማ ሰፊ እና ጥልቀት ያለው ግምገማ ሲያካሂድ ቆይቶ በትናንትናው እለት ባለ 11 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት በድል እና በስኬት ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡

በመድረኩ ከ2000 በላይ የክልል የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን በ15 ዓመታት የተሃድሶ ጉዞ የታዩ ስኬቶችን እና ተግዳሮቶችን ከነ ዝርዝር መንስኤዎቹ በተዘጋጁ  ሰነዶ በመደገፍ በጥልቀት የመታደስ ግምገማ አድርጓል፡፡

በግምገማው ባለፉት 15 ዓመታት በግብርና ምርታማነት፣ በኢንዱስትሪ ልማት መስፋፋት፣ በአገልግሎት ዘርፉ የመጡ ለውጦችን እንዲሁም በትምህርት፣ በጤናና ሌሎች የማህበራዊ ልማት ዘርፎችም የተመዘገቡ ለውጦች አመርቂ መሆናቸውንም ተመልክቷል።

በተለይም በክልሉ ሁለንተናዊና ፈጣን ልማት በማስመዝገብ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማፋጠንና የመልካም አስተዳደር በማስፈን ለውጦች መመዝገባቸው በውይይቱ ተገምግሟል፡፡

ከተገኙ ስኬቶች ባሻገር በክልሉ ባጋጠሙ ተግዳሮቶችና ችግሮች ዙሪያ ሰፊና ጥልቅ ግምገማዎች  መካሄዳቸውን የጠቆመው ብአዴን በተለይ  ከህብረተሰብ ኑሮ መሻሻል ፣ከሥራ አጥነት፣ ከመንግሥት አገልግሎት አሠጣጥ ጋር በተያያዙ ያጋጣሙ ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል ተብሏል ።

የድርጅቱ ውስጠ ዴሞክራሲ፣ የአመራር መሠረታዊ አመለካከት፣ ህዝባዊ ወገንተኝነትና የመንግሥትን ሥልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ፣ትምክህት፣ ጠባብነትና የጥገኝነት አስተሳሰቦችና ተግባራት በአመራሩ የተስተዋሉ በመሆናቸው በኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች  በጥልቀት ግምገማ የተካሄዱባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው ።  

ሌላው በኮንፈረንሱ በጥልቀት ከተገመገሙት ጉዳዮች መካከል የክልሉ ወቅታዊ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች በተለይም በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል የሚገኘውን ወሰን በተመለከተ እንዲሁም የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ዙሪያ የአመራሩ ፈጥኖ ችግር የመፍታት ጉድለቶችና ክፍተቶች ፀረ ሰላም ኃይሎች  አመጽ እንዲቀሰቅሱና በህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳስከተለ ተገልጿል  ።

በክልሉ  በተፈጠሩት  ሁከቶች የትምክህትና የጠባብ ኃይሎች ለዘመናት ተዋደውና ተከባብረው የኖሩትን የአማራና የትግራይ ሕዝቦች መካከል ያልተገባ ጥርጣሬዎችን በመፍጠር ጉዳቶች እንዲደርሱ የፈጠሩት ዘረኛ የቅስቀሳ አካሂያድ ኮንፈረንሱ በዝርዝር በመገምገም አውግዟል፡፡     

በአጠቃላይ በኮንፈረንሱ የተሳተፉ አመራሮች የተስተዋሉ ችግሮችን መንስኤዎች በመለየትና የመፍትሄ ቀመሮች ላይ በመግባባት ለተግባራዊነታቸው በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ተሳታፊዎቹ አረጋግጠዋል ፡፡

በክልሉ የወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያም የተነሱት የህዝብ ጥያቄዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እና ይህንን ሽፋን በማድረግ ስርዓት ለማፍረስ ሌት ተቀን የሚረባረቡ ፀረ- ሰላም ኃይሎችን በተገቢው ሁኔታ በመፋለም የህዝቡን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

በመጨረሻም ብአዴን ባለ 11 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት በዝርዝር በገመገሙት ጉዳዮች ዙሪያ በጥልቀት ለመታደስ ያላቸውን ዝግጁነት እንዲሁም ንቅናቄውን በተሟላ መንገድ ወደ ህዝቡ በማውረድ የወጣቶችን ተጠቃሚነት በዝርዝር የመፍትሄ አቅጣጫዎች ችግሮችን በዘለቄታው ለመፍታት ያላውን ቁርጠኝነት ገልጿል።