መምህራን ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ የምርምር ውጤቶችን በማቅረብ የላቀ ሚና ሊጫወቱ ይገባል ተባለ

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ከመማር ማስተማር ባሻገር ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ የምርምር እና የጥናት ውጤቶችን በማቅረብ የላቀ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ የፌደራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ካሳ ተክለብርሃን ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ባለፉት 25 አመታት በትምህርት ዘርፍ በተመዘገቡ ስኬቶች እና ባጋጠሙ ችግሮች ላይ ትናንት ውይይት አድርገዋል።

ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት መምህራኑ የጥናት ውጤቶችን በማቅረብ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል።

በውይይቱ ላይ ባለፉት 25 አመታት በዘርፉ ከፍተኛ እመርታ መታየቱ ተጠቅሷል።

በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ እንዳለ ከሚታመነው 1 መቶ ሚሊየን ህዝብ ውስጥ 30 ሚሊየን ያክሉ የትምህርት ገበታ ላይ የሚገኝ ነው ተብሏል በመድረኩ ላይ።

የትምህርት ተደራሽነትን ከማስፋት አኳያ ውጤት ቢመዘገብም ጥራትን ማስጠበቅ ላይ ክፍተቶች መኖራቸውም በመድረኩ ተገልጿል።

በተለይም በ1ኛ እና በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ጥራትን በከፍተኛ ሁኔታ ማረጋገጥ ይገባልም ነው የተባለው።

የውይይቱ ተሳታፊ መምህራን በበኩላቸው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መስፋፋታቸው መልካም መሆኑን ጠቅሰው፥ የአመራሮች ምደባ ላይ ያለው ክፍተት መስተካከል አለበት ብለዋል።

ውይይቱ በነገው እለትም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ቀጥሎ ይካሄዳል።(ኤፍቢሲ)