የውይይት መድረኩ ሀሳብ ለማመንጨት እንደሚረዳ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተናገሩ

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የሚደረገው ውይይት በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከመንግስት ጋር ለመነጋገርና ሀሳብ ለማመንጨት እንደሚረዳ ዋልታ ያነጋገራቸው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ፡፡

መንግስት ‹‹የአገራችን ጉዳይ ያገባናል፤ይመለከተናል›› ከሚሉና በሠላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ማድረጉ የተለያዩ ሀሳቦችን ለመለዋወጥ እንደሚረዳ የመላው ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ንቅናቄ(መኢብን) ፕሬዚዳንት አቶ መሳፍንት ሽፈራው ይናገራሉ፡፡

የሥልጣን ተቀናቃኝ ኃይል ከሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መወያየት ፓርቲዎቹ መንግስት ትኩረት ቢሰጥባቸው የሚሏቸውን ሀሳቦች እንዲያቀርቡ ያግዛል ብለዋል፡፡ መንግስትም የተለያዩ ግብዓቶችን ለማግኘት ይረዳዋል፡፡

ፓርቲዎቹ ቢጠናከሩና ቢሻሻሉ የሚሏቸውን ሀሳቦች በማቅረብ ለተሻለ ውጤት እንዲሰራ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ እንደሚስችልም ነው አቶ መሳፍንት የጠቆሙት፡፡

የውይይት መድረኩ ከወቅታዊ ጉዳዮች በተጨማሪ በፖሊሲዎች ላይም ለመምከርና ለመወያየት እንደሚያግዝ የሚናገሩት ደግሞ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ(አንድነት) ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ትግስቱ አወሉ ናቸው፡፡

አቶ ትግስቱ እንዳሉት በውይይት መድረኩ ፓርቲዎቹ በአገሪቱ ልማትና ሠላምን ለማረጋገጥ መንግስት ቢከተል ያዋጣል የሚሉትን አቅጣጫ ይጠቁማሉ፡፡ በመንግስት በኩል ቢሻሻሉና አፋጣኝ መፍትሔ ሊያገኙ የሚገባቸውን ጉዳዮች በተቀናጀ መልኩ ያቀርባሉ፡፡

የኢትዮጵያ ፍትህና ዴሞክራሲ ኃይሎች ግንባር ሊቀ መንበር አቶ ገረሱ ገሣ በበኩላቸው መድረኩ ፓርቲዎች ለወቅታዊ ችግሮች ወቅታዊ የመፍትሔ ሀሳቦችን እንዲሰነዝሩ ያግዛል ይላሉ፡፡

የኢህአዴግ ምክር ቤት ባሳለፋቸው ውሳኔዎች ዙሪያ ማብራሪያ ለማግኘትም ይረዳል፡፡ የውሳኔዎቹን አግባብነትና ተፈፃሚነት በተመለከተም ለመወያየት መድረኩ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ነው አቶ ገረሱ ያረዱት፡፡

የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ አየለ ጫሚሶም የሌሎቹን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና መንግስት የሚገናኙበት የውይይት መድረክ ሃሳቦችን ለማቅረብና ለመወያየት ወሳኝ መሆኑን በመጠቆም፡፡

በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የሚደረገው ውይይትም ተቃዋሚ ፓርቲዎችና መንግስት በመቀራረብ በአገር ጉዳይ ዙሪያ ለመምከር የሚደረግ ውይይት አንዱ አካል ነው ብለዋል፡፡

ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚደረገው ውይይትና ምክክር በቀጣይም ሊጠናከርና ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስምረውበታል፡፡