በሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ኢትዮጵያ 3ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች

በኡጋንዳ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ኡጋንዳን በመርታት በሶስኝነት ውድድሩን አጠናቋል።

ቀን 7 ስአት ከ30 ላይ በጀመረው የደረጃ ጨዋታ ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት አስተናጋጆቹ ሲሆኑ በ5ኛው ደቂቃ ሀሲፋ ናሱማ የግቡ ባለቤት ናት፡፡ ይህ ግብ ለሀሲፋ በውድድሩ ያስቆጠረችው 5ኛ ግብ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ኢትዮጵያ አቻ ለመሆን ብዙ ደቂቃ ያልፈጀባት ሲሆን በ16ኛው ደቂቃ ረሂማ ዘርጋ ሉሲዎቹን አቻ አድርጋለች፡፡

ቡድኖቹ ለእረፍት ከመውጣታቸው በፊት ረሂማ ኢትዮጵያን መሪ ስታደርግ በ73ኛው ደቂቃ ደግሞ ሐት-ትሪክ የሰራችበትን ኳስ ከመረብ አሳርፋለች።

ሎዛ አበራ በ78ኛው ደቂቃ የሉሲዎቹን ቀሪ ግብ ስታስቆጥር የግብ ድምሯን 5 በማድረስ ከከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ተርታ ተሰልፋለች።

ውድድሩ በአሁኑ ሰአት በኬንያ እና ታንዛንያ መካከል የፍጻሜ ጨዋታ እያስተናገደ ይገኛል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)