በአማራና በኦሮሚያ ያጋጣመው ግጭት አንዱ ከወጣቱ ተጠቃሚነት መጓደል የተያያዘ ነው -አቶ ሬድዋን ሁሴን

በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በርከት ያሉ ወጣቶች ችግሩ በማባባስም የችግሩ ሰለባ በመሆንም የሚገለጽ እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ከተጠቃሚነታቸው መጓደል የሚያያዝ መሆኑን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አስገነዘቡ ፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን ለዋልታ እንደገለጹት፤በሁለቱም ክልሎች ያጋጠሙ ሁከቶችና ግጭቶች መነሻው በተለይም ወጣቶች ለነሱ የሚሆን ጥቅም አላገኘንበትም ብለው ካመኑ በግጭቱ ተሳታፊ ለመሆን ስለሚገደዱ ነው ፡፡

እንደሚንስትሩ አባባል በወጣቶችም ሆነ በሌላ ማህበረሰብ ውስጥ የተገኘ ጥቅም ቢኖርም “እኛ ጋ ሲደርስ ተቋርጧል ፤በቂ አይደለም “ ካሉ ይህ የሚፈጥረው ቁጣና ቅሬታ ይኖራል ፡፡

ወጣቶቹ ቅሬታው የማይጠቅማቸውም ቢሆን ነገ የሚስተካከል ሆኖ እያለ አሁን ባለው ተተርሰው ስለሆነ አቋም የሚወስዱት በግርግር የሚሳተፉበትና የችግሩ ሰለባ የመሆን ዕድል ይኖራል ሲሉም ያብራራሉ ፡፡

ዋናው መፍትሔ ወጣቶች በትምህርት በስፋት እንዲታቀፉ ተምረው ሲወጡም ሆነ ከየትምህርት ደረጃቸው ሲያቋርጡ በኢኮኖሚ ውስጥ ትርጉም ያለው ተጠቃሚነት እንዲኖራቸው ለማድረግ የተጀመረውን ስራ ማጠናከር መሆኑን  አስረድተዋል ፡፡

ወጣቱን ለመጥቀም የተደረጉ ሙኮራዎች ቢኖርም ለሁሉም እንዳልተዳረሰ አመልክተዋል ፡፡

ወጣቶች በየዕለቱ ገቢያቸውን ሊያሳድግ የሚችል እንቅስቃሴ ላይ ካሉ ከዚህ ወጣ ብለው መጠቀምና ማግኘት የጀመሩትን ዕድገት ለማደናቀፍ እንቅስቃሴ ላለመግባት ጥንቃቄ ያደርጋሉ ብለዋል ፡፡

ከዚህም ባለፈ ቢቻል ሌሎች ሰዎችም ወደ ግርግር እንዳይገቡ ማስተማርና መከላከል ይጀምራሉ ነው ያሉት ፡፡

ወጣቶች ከሚገኘው ኢኮኖሚ ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወስዱ ከማድረግ ባሻገር የአስተሳሰብ ግንባታ ላይ የሚዛናዊነት ግንባታ ላይ ፣የምክንያታዊ ጥያቄ አቅራቢነትና በጥያቄዎች ትንተና ላይ ተንተርሶ አቋም መውሰድ ላይ ተጨማሪ ስራ የሚያስፈልግ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡