መንግሥት በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴውን አጠናክሮ ይቀጥላል–ፅህፈት ቤቱ

መንግሥት በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ጽህፈት ቤቱ እንዳስታወቀው፤ መንግሥት ሕዝቡ የጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እንዲችል ራሱን በጥልቀት ለማደስ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እያካሄደ ነው።

በዚህም መሰረት መንግሥትን የሚመራው ገዥው ፓርቲ ብሔራዊ ደርጅቶች ራሳቸውን እየፈተሹ መሆኑን ጠቁሞ፤ አደጋውን በመገንዘብ ራስን በጥልቀት ለማደስና አስፈላጊነቱን ለማስረጽ ወደ መካከለኛ አመራር አባላት ወርዶ ውይይት እየተደረገ መሆኑንም አብራርቷል።

ይህ ውይይቱ በቀጣይ ወደ ሕዝቡ ዘንድ እንዲወርድ እንደሚደረግም ጠቁሟል።

በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴው በአጠቃላይ የመንግሥት መዋቅር መሰረታዊ በሆነ ደረጃ ጥገኞችን የማጽዳት ተልዕኮ ያለው መሆኑን መግለጫው አትቷል፡፡

ይህም የበላይ አመራር አባላት ሥልጣንን ለሕዝብ ከማዋል፣ ከተጠያቂነት ጋር የተያያዙትን ችግሮች ለመፈተሽና ለማሰተካከል መሆኑን ፅህፈት ቤቱ አመልክቷል።

አሁን እየተካሄዱ ያሉ ምክክሮች እንደተጠናቀቁ የመንግሥትን ኃላፊነት ለግል ጥቅም ያዋሉ ግለሰቦች በየደረጃው የሚለዩበት ሥርዓት ይዘረጋል።

በዚህ ሂደት ላይም ሕዝቡ አስተያየት እየሰጠበትና መረጃው መጥራቱ እስኪረጋገጥ ድረስ ተመላልሶ የእርምት እንቅስቃሴው እንደሚካሄድ አስታውቋል።

ይህ ሂደት መንግሥታዊ ሥልጣንን ለህዝብ ጥቅም የማዋል የመንግስት የቀደመ ፖሊሲ በአስተማማኝ ደረጃ መመለሱ እስኪረጋገጥ ድረስ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ሕዝብም በንቃት በመሳተፍ የባለቤትነት መንፈስ መረጋገጥ እንዳለበት ጥሪ ቀርቧል።

የኢፌዴሪ መንግሥት የአገልጋይነት ባህሪው እስኪመለስና የተጀመረው ግስጋሴ ዋስትና እስኪያገኝ ድረስ በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጽህፈተ ቤቱ አረጋገጧል።

የኢትዮጵያ ህዝቦችም ለሀገሪቷ የህዳሴ ጉዞ ወሳኝ የሆነውን የመንግስት ውሳኔና እንቅስቃሴ በተለመደው መልኩ መደገፋቸውን በነቃ ተሳትፎ እንዲያረጋግጡ ጥሪውን አስተላልፏል።

መንግሥት ባለፉት ዓመታት የተገኙትን ዘርፈ ብዙና ደማቅ ድሎች ላለማስነጠቅ ውስጡን በጥልቀት ለመፈተሽ መወሰኑን ለአገሪቷ ሕዝቦች ግልጽ ማድረጉ ይታወሳል።(ኢዜአ)