ፖሊስ የመስቀል በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገለጸ

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የመስቀል በዓል በመላ አገሪቱ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ለማድረግ በቂ ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ።

በዓሉ በሰላም እንዲከበር ማህበረሰቡ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግም ጠይቋል።

በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የኮሚሽነር ጄኔራል ጽህፈት ቤት ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር የማነ ገሰሰው እንደገለጹት፥ በዓሉ በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል።

ለመስቀል በዓል አከባበር የፀጥታ ጥበቃ በሚያመች መልኩ የኮማንድ ፖስትም ተቋቁሟል።

ኮማንድ ፖስቱ የተቋቋመው የፌዴራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባና የክልል የፀጥታ ኃይሎች ጋር በተቀናጀ መልኩ መሆኑንም ተናግረዋል።

እንደ ረዳት ኮሚሽነሩ ገለፃ ከወጣቶች፣ ከኃይማኖት አባቶችና ከሚመለከታቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ጋርም ፖሊስ በትብብር ይሰራል።

በበዓላት ወቅት ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ ተብለው የሚጠረጠሩ ነገሮችም ተለይተው መፍትሄ እየተበጀላቸው ይገኛል።

ማህበረሰቡ በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከጸጥታ ኃይሎችና በመላ አገሪቱ ከሚገኙ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ተቋማት ጋር ሊሰሩ ይገባልም ነው ያሉት።

በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ማህበረሰቡ ለፖሊስ ጥቆማና መረጃዎችን በመስጠት የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግም ኃላፊው ጠይቀዋል።

ህዝቡ በበዓሉ ላይ የሚሳተፉ የውጭ አገር ጎብኚዎችን፣ኢትዮጵያን ዳያስፖራዎችንና ሌሎች እንግዶችን በተለመደው የእንግዳ ተቀባይነቱ ሊያስተናግዳቸው ይገባልም ብለዋል።

የመስቀል ክብረ በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የባህልና የሳይንስ ተቋም (ዩኔስኮ) በኢንታንጀብል ቅርስነት መመዝገቡ ይታወሳል።

መስቀል በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን በመላ አገሪቱ በልዩ ልዩ ስነ ስርአቶች ይከበራል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)