የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ምንጩ ስልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል ነው -ህወሓት

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ በክልሉ ለታዩ የመልካም አስተዳደርና ኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ምንጩ የመንግስት ስልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል መሆኑን አስታወቀ፡፡

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ድርጅቱ ከመስከረም ዘጠኝ እስከ 13 ቀን 2009 ዓ.ም ጥልቅ የተሀድሶ ግምገማ አካሂዷል፡፡

በመግለጫው ላይ ለፍትህ መረጋገጥ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለው የክልሉ ሕዝብ በመልካም አስተዳደር እጦት መቸገሩን ኮሚቴው ገምግሟል፡፡

ለቀናት በተካሄደው በእዚህ ግምገማ በክልሉ ያሉትን ጸጋዎች በመጠቀም የወጣቶችን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የተደረገው ትግልና ጥረት ደካማ መሆኑንም አረጋግጧል፡፡

የሕብረተሰቡ ግማሽ አካል የሆኑ ሴቶች ሁሉን አቀፍ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የተደረገው ጥረት ሕብረተሰቡና ድርጅቱ በሚጠብቀው ደረጃ እርካታ አለማምጣቱንም በመግለጫው ላይ ተመልክቷል፡፡

የሥርአቱ አደጋ የመልካም አስተዳደር ችግርና ኪራይ ሰብሳቢነት መሆኑን በግልጽ የተቀመጠ ቢሆንም በክልሉ እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ በሚፈለገው ደረጃ ትግል አለመደረጉን ኮሚቴው ባካሄደው ግምገማ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡

የመንግስት ስልጣንን ለሕዝብ ጥቅምና አገልግሎት ከማዋል ይልቅ ለግል ጥቅምና ክብር ማረጋገጫ ተደርጎ ሲወሰድ መቆየቱንም ድርጅቱ ገምግሟል፡፡

ይህም በክልሉ ለታዩ የመልካም አስተዳደር፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና ሌሎች ችግሮች ዋነኛ ምክንያት ከመሆኑም በላይ ለሕዝብ ምሬት መንስኤ ሆኖ መቆየቱን ማዕከላዊ ኮሚቴው ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡

በድርጅቱ ውስጥ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ተግባራትና መቻቻል እየጎለበቱ መምጣታቸውን የገለጸው የድርጅቱ መግለጫ፣ በእዚህም የድርጅቱ ውስጣዊ ትግል በመፋዘዝ ላይ መሆኑን አመልክቷል።

የህወሓት ማዕካለዊ ኮሚቴ እስከ አሁን ባለፉት ዓመታት የተገኙ ድሎችና የገጠሙ ተግዳሮቶችን በጥልቀት ሲገመግም በድርጅቱ የታዩትን ችግሮች በአጭርና ረጅም ጊዜ ለመፍታት አቅጣጫ ማስቀመጡንም መግለጫው አስረድቷል።

በድርጅቱ ውስጥ የታዩ ተጨባጭ ችግሮችን ለመፍታት በአጭር ጊዜ ቀጣይነት ያለው ውስጣዊ ትግልና የማጥራት ሥራ እንደሚካሄድም ተመልክቷል፡፡

በዚህም የተጠያቂነት መርህን መሰረት በማድረግ በፓርቲው አባላት ላይ ሽግሽግ ለማድረግና የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ መወሰኑን  ኮሚቴው በመግለጫው ላይ አስረድቷል።

በድርጅቱ ውስጥ የሚደረገው ትግል ውጤታማ የሚሆነው የሕዝብ ድጋፍ ሲታከልበት ብቻ እንደሆነ ድርጅቱ ያምናል ሲል ኮሚቴው በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ስለሆነም በድርጅቱ ውስጥ የሚደረገውን ትግል ከተደራጀ የሕዝብ እንቅስቃሴ ጋር ለማስተሳሰር በቀጣይ የሕዝብ ንቅናቄ ለማካሄድ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

መግለጫው እንደሚያስረዳው ከሆነ ህወሓት ከሌሎች እህት የፖለቲካ ድርጅቶችና ሕብረተሰቡ ጋር ተሳስሮ ለመታገልና ለመንቀሳቀስ የሚያስችለውን ውሳኔም አስተላልፏል፡፡

በተጨማሪም ተተኪ አመራር ለማፍራትና ለማብቃት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጋራ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡

ከምሁራን ጋር ይበልጥ ተቀናጅቶ ለመስራትና ለልማታዊ ባለሀብቶች የሚደረገው ድጋፍ  ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ማዕከላዊ ኮሚቴው መወሰኑን መግለጫው አስረድቷል፡፡

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ በቀጣይ ለሚያደርገው ትግልና የማጥራት ሥራም ሕዝቡና የፓርቲው አባል ድጋፍ እንዳይለየው ጥሪ ማድረጉንም የጽህፈት ቤቱ መግለጫ አመልክቷል-(ኢዜአ)፡፡