የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የጀመረውን የጥልቀት ተሃድሶ በማጠናከር ሕዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በተግባር እንደሚመልስ የድርጅቱ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አስታወቁ።
የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሉ ዶክተር አምባቸው መኮንን ትናንት ከክልሉ ውጭ ያሉ የብአዴን ከፍተኛና መካከለኛ አመራር አባላት ግምገማ ሲጠናቀቅ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ ድርጅቱ ጥልቅ ተሃድሶውን እስከ ሕዝቡ ድረስ በማውረድ ችግሮቹን በመፍታት የልማትና የዴሞክራሲ ሥራዎችን ያስቀጥላል።
ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ድርጅቱ ተቀናጅቶ ለመሥራት መዘጋጀቱን የገለጹት ዶክተር አምባቸው፤ ይህም በድርጅቱ አመራር አባላት እምነት ተይዞበት ወደ ተግባር እንደተገባም አስረድተዋል።
ድርጅቱ የገጠሙትን ችግሮችና ፈተናዎች ለመወጣት እንቅፋት የሆኑትን ትምክህትና ጠባብነትን ለመዋጋት መስራት እንደሚያስፈልግም ከመግባባት ላይ መደረሱን አብራርተዋል።
ኪራይ ሰብሳቢነት የሥርዓቱ አደጋ በመሆኑ መዋጋት ጊዜ እንደማይሰጠው በግምገማው ተሳታፊዎች ታምኖበት ወደ ተግባር የሚገባበት አቅጣጫ መዘርጋቱንም ዶክተር አምባቸው ተናግረዋል።
በክልሉ የሚታዩትን ችግሮች በመፍታት የተጀመረውን ሁለንተናዊ እድገት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በጥልቀት በመታደስ የሕዳሴ ጉዞውን ለማፋጠን እንደሚሰሩ ባወጡት ባለሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አረጋግጠዋል።
በፌዴራልና ከክልሉ ውጭ ያሉት አመራር አባላት በአዲስ አበባ “በጥልቀት በመታደስ ክልላዊና አገራዊ ህዳሴያችንን እናረጋግጣለን!” በሚል መሪ ሀሳብ ለአራት ቀናት ያካሄዱትን ግምገማ አጠናቀዋል-(ኢዜአ)፡፡