የጅግጅጋና አከባቢው ነዋሪዎች ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ለመጣል የሚደረጉ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች ከማውገዝ አልፈው በጽናት እንደሚታገሉ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የጅግጅጋ ከተማና የፋፈን ዞን ነዋሪዎች አስታወቁ ።
ከጅግጅጋ ከተማና ከፋፈን ዞን ወረዳዎች የተውጣጡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ለህገ መንግሥቱና ለፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ያላቸውን ድጋፍ ትናንት በጅግጅጋ ከተማ ባካሄዱት የድጋፍ ሰልፍ አረጋግጠዋል።
ህገ-መንግሥቱን መሰረት አድርጎ ተግባራዊ የሆነው የፌዴራሊዝም ሥርዓት የሀገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተከብረው በማንነታቸው፣ ባህላቸውና በሃይማኖታቸው እንዲኮሩ፣ በቋንቋቸው እንዲማሩ፣ እንዲዳኙና እንዲሰሩ ያስቻለ መሆኑን ሰለፈኞቹ በዚሁ ጊዜ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሕዝብም በህገ-መንግሥቱ በተረጋገጠው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ባገኘው ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተጠቅሞ በክልሉ ልማት ቀጥተኛ ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የግብርና፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃና የመሰረተ ልማት አውታሮችን ጨምሮ የዘርፈ ብዙ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውጤቶች ተጠቃሚ መሆናቸውንም አንስተዋል።
የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ከሌሎች የሀገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር ተከባብረው፣ ተቻችለውና ተፈቃቅደው በአንድነት እንዲኖሩ ያስቻለ መሆኑንም አመልክተዋል።
በመሆኑም ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ለመጣል የሚደረጉ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች ከመንግሥት ጎን ሆነው በጽናት ለመታገል ዝግጁ መሆናቸውን በድጋፍ ሰልፉ አረጋግጠዋል።
ሰልፈኞቹ ከያዟቸው መፈክሮች መካከል “የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰብዓዊም ሆነ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ያረጋገጠውን ህግ መንግሥት ለመሸራረፍ መሞከር ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓታችንን መዳፈር በመሆኑ የህይወት ዋጋ እንከፍላለ! ግንቦት7 ኦነግ እና ኦብነግ ፀረ ሰላም ኃይሎች የፌዴራሊዝም ስርዓታችንና የአንድነታችን ጠላቶች ናቸው! ህገ መንግሥታችንን ከማንኛውም ጠላት ለመከላከል ተዘጋጅተናል” የሚሉት ይገኙበታል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሐሙድ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት በአሁኑ ወቅት ፀረ ሰላም ኃይሎች የቀድሞውን ጭቋኝ ሥርዓት ለመመለስ የተለያዩ አፍራሽ እንቅሰቃሴዎችን እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ይህን እኩይ ተግባራቸውን ህዝቡ ለአፍታም መታገስ እንደማይችል አስገንዝበዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ አያይዘውም ንግግር በኢህአዴግና አጋር ድርጅቶቹ ባለፉት 15 ዓመታት የሀገራችንን ህዝቦች ከድህነት ለማላቀቅ በርካታ ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በድጋፍ ሰልፉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የጅግጅጋ ከተማ፣ የአውበሬ፣ ቀብሪበያህ፣ ቱሊጉሌድ፣ ጉርሱምና ጅግጅጋ ወረዳ ነዋሪዎች መሳተፋቸውን ዘግቧል – (ኢዜአ ) ።