የጋምቤላ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ140 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ።
የክልሉ ፍትህ ቢሮ ተወካይ አቶ ኡቶው አብሽሮ እንደገለጹት ፤በክልሉ ይቅርታ ቦርድ ተጣርቶ በክልሉ ፕሬዝዳንት የህግ ታራሚዎች ሙሉ ይቅርታ ተደርጎላቸዋል።
ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች በቆይታቸው የታረሙ በፈጸሙት ድርጊት የተጸጸቱና የበደሉትን ህዝብና መንግሥት ለመካስ ዝግጁ የሆኑ ናቸው ብለዋል።
የክልሉ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ተወካይ ኮማንደር ታደሰ ጉታ እንዳሉት ሙሉ ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች ከፍርዳቸው ግማሽና ከግማሽ በላይ ያጠናቀቁ ናቸው።
ይቅርታው በዘር ማጥፋት፣ በሙስና ፣ በሽብርተኝነት፣ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በሀሰት ገንዘብ ሥራ፣ በአስገድዶ መድፈርና ጠለፋ ፣ በአደገኛ እጽና በደን ጭፍጨፋ የወንጀል ፍርደኞችን አያካትትም ብለዋል።
በተጨማሪም የእርምት ጊዜያቸውን አንድ ሶስተኛውን ለጨረሱ 52 የህግ ታራሚዎች ደግሞ የእርምት ጊዜያቸው በአንድ ሶስተኛ የተቀነሰላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
ለህግ-ታራሚዎች ይቅርታ ማድረግ ያስፈለገው የህዝብና የመንግስትን ጥቅም ለማስከበርና እየተካሄደ ባለው የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ በማሰብ እንደሆነ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ኡኮሌ ኦማን በዚሁ ጊዜ ገልጸዋል።
"ይቅርታ የተደረገላችሁ ታራሚዎች በእርምት ቆይታችሁ ባሳያችሁት መልካም ሥነ-ምግባርና በፈጸማችሁት ወንጀል በመጸጸታችሁና የወንጀልን አስከፊነት የተገነዘባችሁ መሆኑ በይቅርታ አጣሪ ቦርዱ ስለተረጋገጠ ነው" ብለዋል።
በመሆኑም ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ የበደሉትን ህዝብና መንግሥት በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል በክልሉ እየተካሄዱ ባሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች በመሳተፍ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
ከታራሚዎች መካከል አቶ ዴቪድ ኝኮንግ በሰጡት አስተያየት ይቅርታ ተደርጎላቸው ወደ ቤተሰባቸው በመቀላቀላቸው መደሰታቸውን ገልጸው፣ ለመንግሥትም ምስጋና አቅርበዋል።
"በማረሚያ ቤት ቆይታዬም መንግሥት ባመቻቸልኝ ስልጠና የሙያ ባለቤት ሆኛለሁ ፤ ወደ ህብረተሰቡ ስቀላቀል በሰለጠንኩት ሙያ ህዝቡን ለማገልገል በትጋት እሰራለሁ" ብለዋል።
እንዲሁም አቶ ኡኬሎ በቀለ በሰጡት አስተያየት "ወደ ህብረተሰቡ ስቀላቀልም የወንጀልን አሰከፊነት በማስረዳት ዜጎች ወንጀል ከመስራት እንዲታቀቡ ምክሬን እለግሳለሁ ፤ የበደልኩትን ህዝብም ለማገልገል በትጋት እሰራለሁ" ብለዋል – (ኢዜአ ) ፡፡