ስርዓቱ ለሕዝቦች ማንነትና ባህል እኩል ዕውቅናና ጥበቃ ሰጥተዋል -መንግስት ኮሙኒኬሽን

የዴሞክራሲ ስርዓት ለሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነትና ባህል እኩል ዕውቅናና ጥበቃ በመስጠቱ ሕዝባዊ በዓላት እየደመቁ መምጣታቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ጽህፈት ቤቱ 'ሕዝባዊ በዓላት ሕዝብ በባለቤትነት የያዛቸው የትስስራችን መገለጫዎችና የኩራታችን ምንጮች ናቸው' በሚል ትናንት ሳምንታዊ የመንግስት አቋም መግለጫ አውጥቷል ።

አብዛኞቹ ሕዝባዊ በዓላት በአደባባይ የሚከበሩ፣ ሕዝቡ በባለቤትነት ያበለፀጋቸውና በማራኪ ትዕይንቶች የታጀቡ በመሆናቸው የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ቀልብ ጭምር እየሳቡ መሆኑን ገልጿል።

በበዓላቱ ላይ የሚሳተፉ ዜጎች ቁጥርና ድምቀት እየጨመረ መጥቷል፤ አገሪቷ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት ከመሳቧ ጋር ተያይዞም ልዩ የቱሪስት መስህብ በመሆን ላይ ይገኛሉም ብሏል።

በተያዘው ወር ያከበርናቸውና የምናከብራቸው ሕዝባዊ በዓላት የዚህ ዕውነት መገለጫዎች መሆናቸውን ጠቁሟል ።

አገሪቱን በዓለም ልዩ በሚያደርጋት የቀን አቆጣጠር የዘመን መለወጫ እንዲሁም የሙስሊሞች የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓላት በድምቀት መከበራቸውን አመልክቷል።

የክርስትና ዕምነት ተከታዮች የመስቀል ደመራ በዓላቸውን በድምቀት ማክበራቸውን፤ መስከረም 22 ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ የገዳ ስርዓቱ አካል የሆነውን የኢሬቻ በዓል በተመሳሳይ እንደሚያከብርም አመልክቷል።

'በዓላቱ ብዝሃነትን ያከበረ ስርዓት መገንባታችን  ባስገኘልን የልዩነት ውበቶች የምንደምቅባቸው የማንነታችን መገለጫዎችና የኩራታችን ምንጮች ናቸው' መሆናቸውን ጠቅሷል ።

አንዱ በሌላው በዓል ላይ እየተገኘ ልዩነቱን እንደ ውበት በመቁጠር በዓላቱን የጋራ፣ የደስታና የፍቅር አድርጓቸዋል፤ ይህን ተከትሎም የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት ስቧል ብሏል ።

የተባበሩት መንግስታት የሳይንስና ባህል ድርጅት ዩኔስኮ ሕዝባዊ በዓላቱን 'እንደ ዓለም አቀፍ ቅርስ' መዝግቦ ለመንከባከብ ፍላጎት ያሳየው ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም በዚሁ ልክ ሊሳብ የቻለው የኢትዮጵያ ሕዝቦች በማንነታቸውና በባህላቸው ምክንያት ሳይለያዩ ያቆዩዋቸውን በዓላት መንከባከብና ማሳደግ በመቻላቸው መሆኑን ጠቁሟል ።

በመሆኑም በተያዘው ወር የተከበሩና በቀጣይም የሚከበሩ ሕዝባዊ በዓላት 'ማንነታችንን የምንገልፅባቸው፣ ራሳችንን የምናስተዋውቅባቸውና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት እሴቶቻችንን የምናጎለብትባቸው ናቸው' ብሏል

በቀጣይም ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን በሚያጠናክሩ እሴቶች፣ በሠላም፣ በመተጋገዝና ብዝሃነት የሚያስገኘውን ጥቅም በማጎልበት እንዲያከብራቸው ጥሪ አስተላልፏል።

ባለፉት 25 ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዓላቱን በግልና በጋራ፣ በዕኩልነት፣ በድምቀትና በሠላም በማክበር ማንነታቸውን በአደባባይ ሲገልፁ መቆየታቸውንም አንስቷል።

ሕዝባዊ በዓላቱን በባለቤትነት መንፈስ በሠላምና በመከባበር እያከበረ ለሚገኘው ሕዝብ ምስጋና በማቅረብ መንግስት በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ የተጀመሩ ጥረቶችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል ።