በመላ ሀገሪቱ የሦስት ቀናት የሐዘን ቀን ታወጀ 

የኦሮሞ ህዝብ የሰላም፤ የፍቅርና የምስጋና ቀን በሆነው የኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ በተፈጠረ ሁከት ህይወታቸውን ያጡ ንጹሃን ዜጎችን ለማሰብ በመላ ሀገሪቷ ለሦስት ቀናት የሀዘን ቀን መታወጁን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

ፅህፈት ቤቱ ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ጸረ ሰላም ኃይሎች በፈጠሩት ሁከት ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ንጹሀን ዜጎች ለማሰብ ከነገ ጠዋት 12 ሰዓት ጀምሮ በመላ ሀገሪቷ የሦስት ቀናት ሐዘን ታውጇል።

በዚሁ መሰረት የኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ ፀረ-ሰላም ሀይሎች በፈጠሩት ሁከት ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ንጹሀን ዜጎችን ለማሰብ በመላ ሀገሪቱ ሀዘን መታወጁን አመልክቶ፤ በሀገሪቷ በሚገኙ ሁሉም የመንግስት ተቋማት፣ በኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንጽላዎች፤ ትምህርት ቤቶች እና በኢትዮጵያ በተመዘገቡ መርከቦች የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንደሚውለበለብ መግለጫው ጠቁሟል፡፡

በተሻሻለው የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 863/2006 አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ 3 መሰረት በሀገሪቷ ውስጥ አደጋዎች ሲፈጠሩም ሆነ አሳዛኝ ክስተት ሲኖር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሀዘን መግለጫ ይደነግጋል፡፡

ምክር ቤቱ በስራ ላይ ባልሆነበት ጊዜም አፈ ጉባኤው በምክር ቤቱ ስም የሐዘን ቀን እንደሚወስን አዋጁ በድንጋጌው ያመለክታል፡፡