በኦሮሚያ ክልል ሁከት ከተከሰተባቸው ወረዳዎች አብዛኞቹ እየተረጋጉ ነው

በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ከ350 በላይ ወረዳዎች መካከል ሰሞኑን ሁከት የተከሰተባቸው 50 ወረዳዎች ናቸው።

የኦሮሚያ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ምክትል ኮሚሽነር ሰለሞን ታደሰ እንደገለጹት ከ50 ወረዳዎች ውስጥ አብዛኞቹ ወደ መረጋጋት እየተመለሱ ነው።

ምክትል ኮሚሽነሩ በምዕራብ እና ምስራቅ ሸዋ ከሚገኙ ሁለት ወረዳዎች እና ከነገሌ ቦረና አካባቢዎች በስተቀር ሌላው የኦሮሚያ ክፍል ወደ መረጋጋት መጥቷል።

የክልሉ ፖሊስ ከህዝቡ ጋር በመሆን በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ሁከቶችን መቆጣጠር መቻሉን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ፥ ፖሊስ የህዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ መጠቀም ያለበትን ሁሉ ሀይል ይጠቀማል ብለዋል።

በዋናነት ግን ህዝቡ ተረጋግቶ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄዎችን እንዲያቀርብ አቅጣጫ ማስያዝ ላይ ትኩረት ያደርጋል ነው ያሉት።

ምክትል ኮሚሽነር ሰለሞን የተፈጠሩት ሁከቶች ከፖሊስ ቁጥጥር ውጭ የሆኑባቸው ቦታዎች እንደነበሩም አንስተዋል።

 

አብዛኞቹ ሁከቶቹን የተቀላቀሉት አላማውን ያልተገነዘቡ ወጣቶች በመሆናቸው የነገ ሀገር ተስፋዎች በሀይል ማረም ተገቢ ባለመሆኑ ነው ፖሊስ ከፍተኛ ትዕግስት ያሳየው ብለዋል።

ከሰሞኑ ሁከት የተከሰተባቸው አካበቢዎች ከዚህ ቀደም ሰላማዊ የነበሩና ፖሊስ ሰፊ የፀጥታ ሀይል ያላሰማራባቸው በመሆናቸውና ክልሉ ሰፊ የቆዳ ስፋት ያለው መሆኑም በአንዳንድ አካባቢዎች ሁከቶቹ ከቁጥጥር ውጭ ሆነው እንደነበር ጠቁመዋል።

በዚህም የተነሳ የኢሬቻ በዓልን ተከትሎ በተወሰኑ የክልሉ ከተሞች ከፍተኛ የመንግስት እና የግል ንብረቶች መውደማቸውንም ነው የገለጹት።

ህዝብ እና ፖሊስ ተባብረው በሰሩባቸው አካባቢዎች ህዝቡ ወደ ተረጋጋ ማህበራዊ ህይወቱ እየገባ መሆኑንም አመልክዋል።

የፌዴራል ፖሊስም ከክልሉ ፖሊስ ጋር በመጣመር በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ፀጥታ የማስከበር ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል ።

በአጠቃላይ ያለ ህዝብ ተሳትፎ ፀጥታ እና መረጋጋትን ማረጋገጥ አይቻልም ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፥ መላው የኦሮሚያ ህዝብ እንደ ከዚህ ቀደሙ የአካባቢውን ሰላም ለማስፈን ከፖሊስ ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል።

የክልሉ ፖሊስ አሁንም ፀጥታን ከማስከበር ባሻገር የተለያዩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በውይይት እንዲፈቱ ጥረቱን ይቀጥላልም ብለዋል-(ኤፍ.ቢ.ሲ) ።