ብአዴን የተወሰኑ ከፍተኛ አመራሮችን ከማእከላዊ ኮሚቴ አባልነት አገደ፣ማስጠንቀቂያም ሰጧል

የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ብአዴን/ የአመራር ድክመት ባሳዩ የተወሰኑ የአመራር አባላት ላይ ከማእከላዊ ኮሚቴ የማገድ እንዲሁም በሌሎች ላይ የማስጠንቀቂያ እርምጃ መዉሰዱን አስታወቀ፡፡

 

የብአዴን ስራ አስፈፃሚና ማእከላዊ ኮሚቴ ባለፈው አመት ማጠናቀቂያ ላይ በኢህአዴግ ደረጃ የታወጀውን በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ መሰረት በማድረግ ሁለተኛ ስብሰባውን ከመስከረም 21 እስከ 28 ድረስ በነበሩት 8 ቀናት አካሂዶ በማጠናቀቂያዉ ባወጣዉ መግለጫ በተወሰኑ አመራሮች ላይ የከባድ ማስጠንቀቂያና ከማእከላዊ ኮሚቴ አባልነት የማገድ እርምጃ  መዉሰዱን አመልክቷል፡፡

 

ድርጅቱ የህዝቡን ጥያቄዎች በፍጥነትና በበቂ ደረጃ በመፍታት፣ ህዝቡ የመፍትሄው አካል በሚሆንበት አግባብ ችግሮች በወቅቱ እንዲፈቱ በማድረግ በኩል የነበረው የአመራር ጉድለት በቅርቡ ለተከሰተው ክልላዊና አገራዊ ሁኔታ የበኩሉን አስተዋዕኦ ማድረጉን  ቁጭት በተላበሰ የተጠያቂነት መንፈስ ራሱን በመገምገም ዉሳኔ እንዳስተላለፈ ተገልፀል፡፡

 

የመግለጫዉን ሙሉ ይዘት እንደሚከተለዉ አቅርበነዋል፡፡

 

ድርጅታችን ብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴን/ ባለፉት 15 አመታት የአማራ ብሔራዊ ክልል ህዝብን ይሁንታ በማግኘት በአቋቋመው የክልሉ መንግስት አማካይነት በክልሉ የተገኙትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጦች እንዲሁም በሂደቱ ያጋጠሙትን ተግዳረቶችና ችግሮች በጥሞና በመገምገም ለውጡን ማስቀጠል የሚያስችሉ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን እንዳስቀመጠ በአዲሱ አመት ዋዜማ ላይ በሰጠው ድርጅታዊ መግለጫ ለአማራ ክልልና ለመላው የአገራችን ህዝቦች ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ በአንዳንድ የክልላችን ከተሞችና ወረዳዎች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በኤሬቻ በአልና ከዛም በኋላ በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰቱት ሁከቶች በሰላማዊ ሰዎችና በፀጥታ ሃይሎች በደረሰው የሞትና የመቁሰል አደጋ፣ እንዲሁም በህዝብና በመንግስት ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ሃዘንና ፀፀት ተሰምቶታል፡፡

የክልሉ ህዝብ ርካታ ያጣባቸውና ከዚያ በላይ መፍትሄ ሳይሰጣቸው መቀጠል እንደሌለባቸው በምሬት መግለፅ የጀመረባቸውን ትክክለኛ ጥያቄዎች ተገቢ ትኩረት በመሰጥትና በፍጥነት መፍታት እንዳለበት በመወሰን ወደ ንቅናቄ መግባት በጀመረበት ወቅት በክልላችን የተጠሩት የተቃውሞ ሰልፎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄዱ መንግስት ከፍተኛ ጥረት ያደረገ ቢሆንም ሰልፎቹ ሰላማዊ ሆነው እንዲጠናቀቁ በማይፈልጉ ሃይሎች ሁከት ምክንያት በጭራሽ መጥፋት የማይገባው ጥፋት ደርሷል፡፡

የዚህ አይነቱ ሁኔታ በጭራሽ እንዳይደገምና በክልላችን የተጀመረው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ የብአዴን አመራር ከመቸውም ጊዜ ይበልጥ አንድነቱን አጠናክሮና ችግሮችን የመፍታት ብቃቱን አጎልብቶ በቁርጠኝነት ተነስቷል፡፡
የብአዴን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴና ማእከላዊ ኮሚቴ ባለፈው አመት ማጠናቀቂያ ላይ በኢህአዴግ ደረጃ የታወጀውን በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ መሰረት በማድረግ ሁለተኛ ስብሰባውን ከመስከረም 21 እስከ 28 ድረስ በነበሩት 8 ቀናት አካሂዷል፡፡

በዚህ ስብሰባ የብአዴን አመራር በአስራ አምስት አመቱ የተሃድሶ ዘመን የአማራ ብሄራዊ ክልልን በመምራትና በኢህአዴግ አማካይነት በሚካሄደውም አገራዊ አመራር በነበረው ድርሻ ዙሪያ በነበሩት ጥንካሬና ድክመቶች ላይ ከጳጉሜው ስብሰባ የቀጠለ ሰፊና ጥልቅ ግምገማ አድርጓል፡፡
በተሰሩት ስህተቶችና በነበሩት ድክመቶች ላይ እንደአካልና በግለሰብም ደረጃ ተጠያቂነትን መሰረት ያደረገ ሂስና ግለሂስ ተደርጎ ድርጅታችን ቀድሞ እንደነበረው ሁሉ በድክመቶቹ ላይ የማይደራደርና ስህተቱንም በማያዳግም አኳኋን በማረም የክልላችንንና የአገራችንን ህዝቦች ጥቅም በላቀ ደረጃ ለማስከበር በጥልቀት ታድሶና ተጠናክሮ መውጣቱን አረጋግጧል፡፡
ቀደም ሲል ከማእከላዊ ኮሚቴው በተሰጡት መግለጫዎች በገሃድ እንደተገለፀው ሁሉ በድርጅታችን አመራር ድክመት ምክንያት በህዝባችን ዘንድ ለተፈጠረው ቅሬታ ዋነኛ ተጠያቂው የድርጅታችን ከፍተኛ አመራር ነው፡፡

በክልላችን እያደገ ከመጣው ኢኮኖሚ ልማት በበቂ ደረጃ ተጠቃሚ ያልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸው፣ ከራሱ እድገቱ የሚመነጩ የፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን እንዲሁም በአቋራጭ ለመክበር የተመቸው የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚን በመናድና መልካም አስተዳደርን በማስፈን በኩል ብአዴን በሚመራው የክልሉ መንግስት አማካይነት የተለያዩ ጥረቶች ያደረገ ቢሆንም ጥረቶቹ ካለው ችግር ጋር የማይመጥኑና በጣም የሚዘገዩ በመሆናቸው ምክንያት የህዝቡን ርካታ ማረጋገጥ አልቻሉም፡፡

የህዝቡን ጥያቄዎች በፍጥነትና በበቂ ደረጃ በመፍታት፣ ህዝቡ የመፍትሄው አካል በሚሆንበት አግባብ ችግሮች በወቅቱ እንዲፈቱ በማድረግ በኩል የነበረው የአመራር ጉድለት በቅርቡ ለተከሰተው ክልላዊና አገራዊ ሁኔታ እንዳበቃን የብአዴን አመራር ቁጭት በተላበሰ የተጠያቂነት መንፈስ ራሱን ሂስ አድርጓል፡፡
በተወሰኑ አመራሮች ላይም የከባድ ማስጠንቀቂያና ከማእከላዊ ኮሚቴ አባልነት የማገድ እርምጃ ወስዷል፡፡

የክልላችን ህዝብ ያነሳቸውን ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ፣ ወቅታዊ ሁኔታውን ለመለወጥ፤ የሰላም፣ የልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታችንን አጠናክረን ለመቀጠል የሚያስችሉንን እቅዶች በማፅደቅ ስብሰባውን አጠናቋል፡፡

ውድ የብአዴን አባላት!
በማእከላዊ ኮሚቴያችን የተጀመረው በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ በርግጥም ድርጅታችንን የማደስና የማጠናከር ብቃት ሊኖረው የሚችለው መላ የድርጅታችን አባላት የተሃድሶው አካል ሆነው ሲንቀሳቀሱ ብቻ ነው፡፡

በዚህ ረገድ በቅርቡ በየዞኑ የተካሄደው ኮንፈረንስ በየወረዳውና በየአደረጃጀቱ እንዲቀጥልና ሁሉም አባላት እንዲሳተፉ ይደረጋል፡፡
የተሃድሶው መሰረታዊ አቅጣጫ የህዝብን ጥቅም በማስቀደም ራሰህን ማረም በመሆኑ መላ የድርጅታችን አባላት ድክመቶቻቸውን በመታገል ብቁ የተሃድሶ ሃይል ሆነው እንደሚወጡ የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ ይተማመናል፡፡ ድርጅታችን መልካም ተመክሮዎቹን እያቀበ፣ ድክመቶቹን እያረመና የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች በፅናት እያለፈ ለድል የመብቃት ልምዱና በዚህ ሂደትም ያዳበራቸው እሴቶች በጥልቀት ለመታደስ የተጀመረው ንቅናቄያችን ግብአቶች ሆነው ሊያገልግሉን ይገባል፡፡ የድርጅታችንን ወርቃማ እሴቶች ጠብቀን እንዳለፉት አመታት ሁሉ ዛሬም ሌላ አኩሪ ታሪክ ለማስመዝገብ እንድንነሳ የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ ለመላ የድርጅታችን አባላት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የተከበራችሁ የአማራ ብሔራዊ ክልል ህዝቦች!
ብአዴን መላ ህይወታቸውን ለህዝቦች ጥቅም አሳልፈው በሰጡ ቆራጥ የህዝብ ልጆች አፅም ተማግሮ በደማቸው ተለስኖ የቆመ ህዝባዊና አብዮታዊ ድርጅት ነው፡፡
ባለፉት ሰላሳ አምስት የትግልና የድል ጉዞዎቹ እንደሚመሰክሩት ስህተት አልሰራም ብሎ የማይመፃደቅ፣ የሚሰራቸው ስህተቶች ግን ስትራተጅያዊ ዝንፍትን የማያስከትሉ መለስተኛ ስህተቶች ብቻ እንዲሆኑ፣ የሚፈፅማቸው መለስተኛ ስህተቶችም ቢሆን የማይደጋገሙና በፍጥነት የሚታረሙ እንዲሆኑ አበክሮ ሲሰራ የቆየ ድርጅት ነው፡፡

እነሆ ዛሬም በዚህ አቅጣጫ በመጓዝ ላይ ይገኛል፡፡ የብአዴን አመራር ስህተት መስራቱን ያምናል፤ የተሰራው ስህተት ህዝባዊነቱን ሙሉ በሙሉ የሚንድና ከጎዳናው የሚያወጣው እንዳይሆንና እንዳይደገም ለማድረግ ጠንካራ የሃሳብና የተግባር አንድነት ገንብቶ ተነስቷል፡፡
እስካሁን የዘገየበትን በሚያካክስ ፍጥነት በመንቀሳቀስም ስህተቶቹን ለማረምና ችግሮቹን ለመፍታት፣ የህዝቡ ጥያቄዎች ተገቢ መልስ እንዲያገኙ ብቁ ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
የብአዴን አመራር ያላንዳች ማወላወል የተቀበለውን ተጠያቂነት መሰረት በማድረግ የድርጅትና የመንግስት አመራሩን መልሶ ያደራጃል፡፡

የመልሶ ማደራጅቱ ዋነኛ ይዘትም በአደረጃጀትና በአሰራር፣ በአመራር ሃላፊነት ላይ የሚቀመጡ ሰዎች ቅኝትና ተጠያቂነት፣ እንዲሁም ህዝቡ አመራሩን በመቆጣጠርና በመግራት ላይ በሚኖረው ሚና ዙሪያ ያተኮረ ይሆናል፡፡
የጀመርነው በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ በቃደለት አቅጣጫ እንዲጓዝ በማድረግ በኩል ዛሬም እንዳለፉት አመታት ሁሉ የክልላችን ህዝቦች በድርጅታቸው አመራር ላይ እምነት በማሳደር ከጎናችን እንዲሰለፉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

በድርጅትና በመንግስት አመራችን ድክመት ምክንያት በድርጅታችንና በህዝባችን መካከል የተፈጠረውን መለስተኛ ክፍተት እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ክልላችንና አገራችን የጀመሩትን እድገት በማደናቀፍ አልፈነው መምጣት ወደጀመርነው ስንዴ ለማኝነት ለመመለስና አገራችንን አገራዊ ጥቅሟን ማስከበር የማትችል ደካማ አገር ለማድረግ የሚሯሯጡ ሽብርተኞችንና ፀረ ሰላም ሃይሎችን ከመንግስት ጎን በመቆም እንድትፋለሙዋቸው የብአዴን አመራር ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የተከበራችሁ የአማራ ክልል ወጣቶች!
ባለፉት አስራ አምስት አመታት በክልላችን ውስጥ ሰፊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት እንደተመዘገበና አስተማማኝ ሰላም ሰፈኖ እንደቆየ በሂደቱም በርካታ ወጣቶች ተጠቃሚ መሆን እንደጀመሩ ቢታወቅም የሚገባችሁን ያህል ገና ተጠቃሚዎች እንዳልሆናችሁ የብአዴን አመራር በፅኑ ያምናል፣ በዚህም ራሱን ወቅሷል፡፡
ይህንን መሰረት በማድረግም ለወጣቱ የስራ እድል የመፍጠር ጉዳይን በጥልቀት ከመታደስ ንቅናቄያችን ዋነኛ አጀንዳዎች አንዱ አድረገን መክረንበታል፡፡ በሁሉም የክልላችን ገጠሮችና ከተሞች የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችና እቅዶችን ነድፈናል፡፡

በስራ እድል ፈጠራ መስክ ባለፉት አመታት የተገኙትን መልካም ተመክሮዎች በማዳበርና ተጨማሪ አዳዲስ አቅጣጫዎችን በማካተት ሰፊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ተዘጋጅተናል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በ2ዐዐ9 ዓ.ም አመታዊ እቅዱ ላይ ዝርዝር የስራ እድል ፈጠራ ስራዎችን አቅዶ ወደ ተግባር ለመግባት ያደረገው ዝግጅት ሊሳካ የሚችለው ከሁሉ በላይ የክልላችን ወጣቶች ንቁ ተሳትፎ ከታከለበት ብቻ እንደሆነ የብአዴን አመራር ያምናል፡፡
ወጣቶች ችግሮች እንዲፈቱላቸው መጠየቅ ብቻ ሳይሆን የመፍትሄው አካል ሊሆኑ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ የክልላችን ወጣቶች መንግስት ጥያቄዎቻቸውን ለመመለስ የሚያደርገውን ጥረት መደገፍ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ የህዝቡና የወጣቱ ጥያቄዎች መልስ የሚያገኙት በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ብቻ እንደሆነ የማያዳግም አቋም መያዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በክልላችንና በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች እንደታየው አሸባሪዎችና አፍራሽ ሃይሎች መጠቀሚያ የሚያደርጉት ወጣቶችን በመሆኑ ራሳቸውን ከጥፋት ሃይሎች ስምሪት ማራቅ ይኖባቸዋል፡፡
በዚህ አጋጣሚ አብዛኛው የክልላችን ወጣቶች ተገቢ የሆነውን ጥያቄና አገርን ለማፈራረስ የተወጠነውን የጥፋት ድግስ በትክክል በመለየት ለሰላም፣ ለህግና ስርዓት መከበር ያሳዩትን ፅኑ አቋም የብአዴን አመራር ያደንቃል፣ ለእንደነዚህ አይነት ወጣቶች ያለውንም አክብሮት መግለፅ ይወዳል፡፡

የተከበራችሁ የክልላችን የመንግስት ሰራተኞችና ምሁራን!
በአገራችንና በክልላችን የተመዘገቡት ለውጦች የመንግሰት ሰራተኞችና በተለያዩ የሙያ ዘርፍ የተሰማራችሁ ምሁራን ጥረትና ተሳትፎ የተገኙ ውጤቶች በመሆናቸው ለውጦቹ እንዲቀጥሉ ብቻ ሳይሆን ስር እንዲሰዱ በማድረጉም በኩል የእናንተን የማይተካ ሚና እንደሚጠይቅ የብአዴን አመራር ያምናል፡፡

ከዚህም በመነሳት ሁለንተናዊ ተሳትፎአችሁን ማጠናከርና የእንናተ የሆኑትን ጥያቄዎች በፍጥነት መመለስ ስለሚቻልበት አግባብ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄው አንዱ አጀንዳ አድርጎ መክሯል፡፡
በሌሎች መስኮች እንደታየው ሁሉ የእናንተን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል የብአዴን አመራር ድክመት እንደነበረበት ገምግሟል፡፡

ይህንን ሁኔታ መለወጥ የሚቻለበትን አግባብ አስመልክቶም የቀጣይ ተግባራትን አቅጣጫ አስቀምጧል፣ እቅድም አዘጋጅቷል፡፡ በሁሉም ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ከብአዴን/ኢህአዴግ ጋር አንድ አይነት አመለካከት ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ የፖለቲካዊ ልዩነት ገንቢ የሆነው የልዩነት መፍቻ መንገድ ግን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ውይይት እንጂ ሃላፊነት የጎደለው የዜሮ ድምር ጨዋታ ከቶ እንደማይሆን የጋራ መግባባት ሊያዝበት ይገባል፡፡

በዚህ አጋጣሚ የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ በክልላችን የሚገኙ አብዛኛዎቹ የመንግስት ሰራተኞችና ምሁራን የድርጅታችንን ድክመቶችና ጥንካሬዎች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ በመገምገም ላቀረቡልን ሂስና ድጋፍ ያለውን አክብሮት ይገልፃል፡፡

በቀጣይ በሚካሄዱ የምክክር መድረኮችም ገንቢ ተሳትፎ በማድረግ ድርጅታችን የጀመረው በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ እንዳለፉት አመታት ሁሉ አንፀባራቂ ድሎችን በማስዘመዝገብ እንዲጠናቀቅ ከብአዴንና የክልሉ መንግስት ጎን እንድትሰለፉ ጥሪያውን ያቀርባል፡፡
በጥልቀት በመታደስ ክልላዊና አገራዊ ህዳሴያችንን እናፋጥን!
የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ
መስከረም 29/2ዐዐ9 ዓ.ም
ባህርዳር