በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተነሱ የማንነት ጥያቄዎች በዚህ አመት ሙሉ በሙሉ ምላሽ ያገኛሉ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች የተነሱ የማንነት ጥያቄዎች በህገ መንግስቱ መሰረት በተያዘው ዓመት ሙሉ ለሙሉ ምላሽ ያገኛሉ አለ።

ምክር ቤቱ 5ኛ የፓርላማ ዘመን ሁለተኛ ዓመት አንደኛ መደበኛ ስብሰባውን ትናንት ያካሄደ ሲሆን የ2009 በጀት ዓመት ዕቅድንም አፅድቋል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ያለው አባተ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፥ እስካሁን ሳይመለሱ የቆዩ የማንነት ጥያቄዎች በሙሉ በዚህ ዓመት ምላሽ ያገኛሉ።

እስካሁን የተነሱ ጥያቄዎች በአብዛኛው ከመልካም አስተዳደር ጉድለት፣ ከታሪካዊ አመጣጥና ከግለሰብ ፍላጎት ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ያነሱት አፈ ጉባኤው፥ ሁሉም በህገ መንግስቱ መሰረት ምላሽ ያገኛሉ ብለዋል።

ለተነሱ ጥያቄዎች ፈጣን መልስ ለመስጠት እንዲቻልም ጥያቄው በየክልላቸው እየታዩና አግባብነታቸው እየተጠና መሆኑን ገልፀዋል።

ምክር ቤቱ በበጀት ድጎማና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን የ2009 በጀት ዓመት ዕቅድም አፅድቋል።

ዕቅዱም ወቅታዊ የክልሎችን የእድገት ሁኔታ በማገናዘብ፣ፍትሃዊ የገንዘብ ድጎማና የሃብት ክፍፍልን ትኩረት ያደረገ ነው ተብሏል።

ዕቅዱ በ2010 ዓ.ም ተግባር ላይ የሚውል አዲስ የበጀት ድጎማና የገቢዎች ድልድል ቀመር ዝግጅት ተካቶበታል።

የቋሚ ኮሚቴው ፀሃፊ አቶ ሃይሉ ይፋ እንዳሉት እስካሁን ሲሰራበት የነበረው የበጀት ክፍፍልና ድጎማ ቀመር በዚህ ዓመት መጨረሻ አገልግሎቱን ይጨርሳል።

አዲሱን ቀመር ለማዘጋጀት የሃሳብ ማሰባሰብ፣ የአማካሪዎች ቅጥር መፈፀምና ክልሎችን የማሳተፍ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ