የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የመንግሰት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በጋራ በመሆን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ፥ የአውሮፓ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና የአሜሪካ አምባሳደሮችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታወጀው ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠትና የተመቸ ሁኔታን ለመፍጠር እንጂ ከህብረተሰቡ የተነሱ ጥያቄዎችን ለማፈን አለመሆኑን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል።
አቶ ጌታቸው አያይዘውም የውጭ ኃይሎች እጅ መኖሩ ችግሩን እንዳወሳሰበው ጠቁመው፥ እነዚህ ኃይሎች በአንዳንድ አካባቢዎች በሞተር ሳይክል የታገዘ ጥቃት እያደረሱ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ የተንቀሳቃሽ ስልክ መጠን እና ቅርጽ ያላቸውን የእጅ ቦምቦች በመያዝ መንቀሳቀሳቸውንም አንስተዋል።
አቶ ጌታቸው በማብራሪያቸው በመንግስት የሚካሄደው የመዋቅር ማሻሻል ተፈጻሚ እንደሚሆንም ነው የተናገሩት።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ በበኩላቸው፥ የህዝቦች ጥያቄ ሌላ አላማ ባላቸው ቡድኖች መጠለፉን ገልጸዋል።
ሁኔታው ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ኢላማ ያደረገ መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደር ታዬ፥ ለዘመናት የቆየው የህዝቦች አብሮ የመኖርና የመቻቻል ባህል ላይ ተፅዕኖ የፈጠረ መሆኑንም ነው የገለጹት።
መንግስትም የተፈጠረውን ሁከትና ብጥብጥ ለመቆጣጠር እና ሃገሪቱን ወደቀደመ ሰላሟ ለመመለስ በማለም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁን አስረድተዋል።
የማህበራዊ ሚዲያ እና ኢንተርኔት ስለመቋረጡ ለተነሳው ጥያቄ በሠጡት ምላሽም፥ መንግስት ቅድሚያ ለደህንነት እና ለፀጥታ መስጠቱን ነው የጠቀሱት።
የተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ በማህበራዊ ሚዲያ በሚነዙ አሉባልታዎች መባባሱን በማስረዳት።
በማብራሪያው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሃገሪቱ ከፌደራል እስከ ታችኛው አወቃቀር ያሉ የፀጥታ ሃይሎችን በአንድ ትዕዛዝ ስር በማድረግ በሃገሪቷ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለማስቆም ያለመ መሆኑ ተነስቷል።
ማብራሪያው መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የሌሎች ሃገራት ዲፕሎማቶች ከሰዓት በኋላም የሚሰጥ ይሆናል።(ኤፍ ቢ ሲ)