የኦነግ ዓላማ ለማስፈጸም ተንቀሳቅሰዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች ተከሰሱ

አሜሪካ ከሚገኘው የኦነግ የሽብር ቡድን ከፍተኛ አመራር ጋር የስልክ ግንኙነት በማድረግ አባላትን በመመልመልና ስልጠና ለመስጠት የተጠረጠሩ 17 ግለሰቦች ክስ መመስረቱን ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ ።

ተጠርጣሪዎቹ ከሽብርተኛው ኦነግ አመራር ገንዘብ በመቀበል በአዲስ አበባና በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች በመንቀሳቀስ የተጠረጠሩት ግለሰቦቹ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛው የሽብር ወንጀል ችሎት ቀርበው ክሳቸው መነበብ መጀመሩን ገልጿል ።

ክሱ የተመሰረተባቸው ተከሳሽ ድሪብሳ ዳምጤ እና ሰኚ ዱጋሳን ጨምሮ 17 ግለሰቦች ነዋሪነታቸው አዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱ፣ ሰበታ፣ ጅግጅጋ እና በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ያደረጉ ናቸው ብሏል ።

ከሽብር ቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ግንኙነት በማድረግ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የሽብር ቡድኑን ተልዕኮ በመቀበል ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል የሚለው በክሱ ጠቅሷል።

በሀገር ውስጥ አባላትን በመመልመልና በማደራጀት የኢትዮጵያን መንግስት በትጥቅ ትግል በሀይል የመለወጥ የፖለቲካ አላማ በመያዝ የሀገሪቱን ህገ መንግስታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተቋማትን ለመናድ እና ለማፈራረስ ሲሰሩ እንደነበርም በክሱ አስረድቷል ።

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ጫካዎችን በማጥናት፣ ወታደራዊ ካምፕ በመመስረት እና አባላትን በህዋስ በማደራጀት ወታደራዊ ስልጠና ሰጥተዋል ነው ያለው በክሱ።

ይህን አላማቸውን ለማሳካትም አሜሪካ ከሚገኙ የኦነግ የሽብር ቡድን ከፍተኛ አመራሮችና ከጀዋር መሀመድ ጋር የስልክ ግንኙነት በማድረግ ለስልጠና እና ለሽብር ተግባራቸው መፈጸሚያ በተለያዩ ጊዜያት 157 ሺህ ብር መቀበላቸው ጠቁሟል።

በተቀበሉት ገንዘብም አዲስ አበባ ልዩ ቦታው አውቶብስ ተራ አካባቢ በመሄድ ለጊዜው ማንነቱ ካልታወቀ ግለሰብ ሶስት ክላሽ የጦር መሳሪያ ከ95 ጥይት ጋር በመግዛት በምዕራብ ሸዋ ዞን በሚገኝ አፋ ጫካ በመግባት ወታደራዊ የአካል ብቃት ስልጠናን ጨምሮ የመሳሪያ መፈታታት እና መገጣጠም እንዲሁም የተኩስ ኢላማ ስልጠና መስጠታቸው ነው በክሱ የተመለከተው-(ኤፍ.ቢ.ሲ)።