በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት የወጣ የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃ አፈፃጸም መመሪያ ይፋ ሆነ።
ኮማንድ ፖስቱ በአዋጁ ልዩ ክልከላ የተደረገባቸው የቀይ ዞኖችን በዝርዝር ለይቷል።
በአገሪቱ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅብረሰብ አባላትም ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ክልል ውጭ ያለ ፍቃድ የማይንቀሳቀሱ ይሆናል።
የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያትና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃ አፈፃጸም መመሪያውን ይፋ አድርገዋል።
ኮማንድ ፖስቱ በተወሰኑ አካባቢዎች እንዳይፈጸሙ የተከለከሉ ድርጊቶች የተለዩባቸው ቀይ ዞኖችን በይፋ አሳውቀዋል።
በዚህ መሰረት በሁሉም የአገሪቱ የድንበር አቅጣጫዎች 50 ኪሎ ሜት ወደ ውስጥ ገባ ብሎ በቀይ ዞን መለየቱን ተናግረዋል።
በአገሪቱ ከሚገኙ ዋና ዋና መንገዶች 25 ኪሎ ሜትር ወደ ግራና ወደ ቀኝ በቀይ ዞን ተከልለዋል።
ከአዲስ አባባ ጂቡቲ፣ ከአዲስ አበባ ሻሸመኔ-ዶሎ፣ ከአዲስ አበባ ሐረር፣ ከአዲስ አበባ አሶሳ፣ ከአዲስ አበባ ጋምቤላ፣ ከአዲስ አበባ ገብረ ጉራቻ፣ ከጎንደር መተማ፣ ከጎንደር ሑመራ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ሻሸመኔ-ሞያሌ የሚወስዱ ዋና ዋና መንገዶች በቀይ ዞን ተለይተዋል።
በቀይ ዞንነት በተለዩ አካባቢዎች የጦር መሣሪያ፣ ስለት ወይም እሳት የሚያነሱ ነገሮችን ከመኖሪያ ቅጥር ግቢና ከይዞታ ውጭ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ በኢኮኖሚ አውታሮች፣ በመሰረተ ልማቶችና በኢንቨስትመንት ተቋማት፣ በእርሻ ልማቶች፣ በፋብሪካዎችና በመሰል የልማት ተቋማት አካባቢ ከቀኑ 12 ሰዓት በኋላ እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ ከተፈቀደለት ሰራተኛ በስተቀር መንቀሳቀስ የተከለከለ ሆኗል።
ይህን የሰዓት እላፊ ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ሰው ላይ የጥበቃ ወይም የሕግ አስከባሪ አካላት እርምጃ እንዲወስዱ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል።
ሁከትን ለማስቆምና አደጋን ለመከላከል በፀጥታ ኃይሎች የሚደረግ እንቅስቃሴን ማወክ አይቻልም።
በተለዩት ቀይ ዞኖች ሠላምና ፀጥታ ሊያደፈርሱ ይችላሉ ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች እንዲሁም ለጉዳት ተጋላጭ ናቸው ተብለው የሚገመቱ ሰዎች ወይም ቡድኖች በተወሰነላቸው በአንድ አካባቢ እንዲቆዩ ወይም እንዳይገቡ ሊከለከሉ ይችላሉ።
ለአካባቢው ደህንነት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ወደ ተዘጋ መንገድ ማንም ሰው እንዳይገባ ኮማንድ ፖሰቱ የሰጠውን እግድ ወይም ክልከላ መተላለፍ ክልክል ነው።
በወጣው የአፈፃጸም መመሪያ የኮማንድ ፖስቱ እውቅናና ፈቃድ ሳያገኙ ዲፕሎማቶች ለራሳቸው ጥበቃና ደህንነት ሲባል ከአዲስ አበባ ከ40 ኪሎ ሜትር ክልል ውጭ የማይንቀሳቀሱ ይሆናል።
በተጨማሪ ከስደተኛ ካምፕ አግባብ ካለው አካል ከሚሰጥ ፈቃድ ውጭ መውጣት ወይም ሕጋዊ ቪዛ ሳይኖረው ወደ አገር ውስጥ መግባት የተከለከለ ሆኗል።
ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የአገርን ሉአላዊነት፣ ደህንነትና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚጎዳ ጋዜጣዊ መግለጫ ለውጭና ለአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን መስጠት አይችልም።
ከውጭ መንግሥታት ወይም ከውጭ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር የአገርን ሉአላዊነት፣ ደህንነትና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ሊጎዳ የሚችል ግንኙነትና የመልዕክት ልውውጥ ማድረግም ተከልክሏል።
በህዝባዊና ብሔራዊ በዓላትን ማወክ እንዲሁም በኃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ሕዝባዊ በዓላት ላይ ቅስቀሳ ማድረግም አይቻልም።
የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ማወክ፣ መንገድ መዝጋትና በዛቻ ሠላማዊ እንቅስቃሴ ማወክና አገልግሎት ማስተጓጎል እንዲሁም የመጓጓዣ ታሪፍ መጨመር የተከለከለ ነው።
ማንነትን ወይም ዘርን መሰረት ያደረገ ማንኛውም ዓይነት ጥቃት መፈፈጸም ወይም ጥቃት እንዲሁም የሚያነሳሳ ንግግር መናገር የተከለከለ ነው።
በትምህርት ተቋማትና በስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች አድማ ማድረግና ሁከቶች መፍጠርና በተቋማት ጉዳት ማድረስ ተከልክሏል።
በሽብር ከተሰየሙ ድርጅቶችና ከፀረ-ሠላም ኃይሎች ጋር ግንኙነት ማድረግና የነሱ ጽሁፎች መያዝ፣ ማሰራጨት፣ አርማቸውን መያዝ ወይም ማስተዋወቅ የተከለከለ ነው።
የአሸባሪ ድርጅቶች የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ሥርጭቶችን ማሳየትና ማስደመጥ እ ንዲሁም መከታተልና ሪፖርት ማድረግ የተከለከለ ሆኗል።
የህዝብና የዜጎች ሠላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ሲባል ከኮማንድ ፖስቱ ፈቃድ ውጭ ማንኛውም ሰልፍና የአደባባይ ስብሰባ በመላው አገሪቱ ማካሄድ አይቻልም። (ኢዜአ)