የሀገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ ክብር ለማስጠበቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ገለፁ

አፍራሽ ተግባራትን በመከላከል የሀገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ ክብር ለማስጠበቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

በከተማዋ ዘጠኙ ቀበሌዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ዘጠነኛውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓልን ትናንት በፓናል ውይይት አክብረዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ነዋሪዎች ሰንደቅ ዓላማ የማንነታቸው መገለጫና የብሔሮች ብሔረሰቦች እኩልነት ማረጋገጫ በመሆኑ ክብርና ዝናውን ለማስጠበቅ እንደሚጥሩ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡

ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ሉዓላዊነት ማሳያ መሆኗን ጠቅሰው፤ የቀኑ መከበር በሰንደቁ ስር ብሔር ብሔረሰቦች በጋራ ተከባብረውና አንድነታቸውን ጠብቀው ለሀገር ዕድገትና ልማት እንዲረባረቡ የሚያጠናከር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቅርብ ጊዜ ወዲህ የህዝቦች እኩልነትና በጋራ መኖርን እንዲሁም የሀገር መሰረተ ልማትን  በማፈራረስና በማውደም ተግባር ላይ የተሰማሩ ፀረ-ልማትና ፀረ-ሰላም ድርጊቶች ኮንነዋል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ድርሻዬ መኩሪያ የሰው ህይወት የሚቀጥፍ ተግባር ፣ የተገነቡ ልማቶችን የሚያፈርሱ ፀረ-ልማት አካላትን አጥብቀው አንደሚያወግዙ ተናግረዋል፡፡

"ወጣቱ ከነዚህ የፀረ-ልማትና የፀረ- ሰላም ኃይሎች በመራቅ በሰንደቅ ዓላማ ሥር ተሰብስቦ ለሀገር ዕድገት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል "ብለዋል፡፡

" ሰንደቅ ዓላማችን የኢትዮጵዊነታችን መለያ አርማው ነው ፤ የማንነታችን መገለጫ ነው" ያሉት ደግሞ አቶ ረሺድ ሐሰን ሲሆኑ የማንነት መገለጫ ሰንደቅ የሆነው አርማ በፀረ- ሰላምና ከፀረ-ልማት ኃይሎች መጠበቅ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡፡

እንደ ነዋሪዎቹ ገለፃ የሰንደቅ አላማ ምንነትን በስፋትና በጥልቀት ለአዲሱ ትውልድ በማስተማርና በማሳወቅ  ወጣቱ ልክ እንደ አባቶቹ ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር የድርሻውን እንዲያበረክት ማድረግ ይገባል፡፡

የአፍራሽ ሃይሎችን ተግባራትን በመከላከል የሀገሪቱን ሰንደቅ ዓላማን ክብርና መገለጫቸውን ለማስጠበቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አብደላ አህመድ "ሰንደቅ ዓላማችን የልማት፣የሰላም፣የዴሞክራሲ ሥርዓት መገለጫና የቀድሞ ታላቅ ታሪካችንን የሚያስታውስ ጭምር ነው " ብለዋል፡፡

በዚህ አርማ ሥር በጋራ በመሰባሰብ የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ከዳር ማድረስ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

በዓሉ በድሬደዋ ከተማ " ሰንደቅ  ዓላማችን የሉኣላዊነታችን መገለጫ በብዝሃነት ላይ ለተመሰረተው አንድነታችን አርማ ነው"  በሚል መሪ ሃሳብ በፅዳት፣ በስፖርታዊ ውድድር እንዲሁም  ስለሰንደቅ ዓላማ ግንዛቤ በሚያስጨብጡ የጥያቄና መልስ ውድድሮች መከበሩን ቀጥሏል(ኢዜአ) ፡፡