ባለስልጣኑ የቴሌቭዝን፣የሬዲዮ ጣቢያና የሴት አፕ ቦክስ ማምረት ፍቃድ ሰጠ

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ለሶስት ቴሌቭዥን ጣቢያዎች ፣ለሶስት ሬዲዮ ጣቢያዎችና ለሁለት ሴት ቶፕ ቦክስ አምራች ተቋማት ፍቃድ ሰጠ፡፡

ባለሥልጣኑ ዛሬ በሸራተን አዲስ ፈቃድ ከሰጣቸው ብሮድካስተሮችና አምራቾች ጋር የፍቃድ አሰጣጥ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ፍቃድ የተሰጣቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል፣ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና አርኪ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ ሲሆኑ ዋን ላቭ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ(ሉሲ ሬዲዮ)፣ አርኪ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ(አሀዱ ሬዲዮ) እና ኤዲስቴለር ትሬዲንግ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ፍቃድ አግኝተዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የቴሌቭዥን ጣቢያዎችን ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር ሴት ቶፕ ቦክስን በአገር ውስጥ ለማምረት ለጣና ኮሙኒኬሽን እና በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የሃይ ቴክ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ፍቃድ ተሰጥቷል፡፡

በፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተገለፀው የብሮድካስተርነትና የአምራችነት ፍቃድ የተሰጣቸው ተቋማት ባቀረቡት ፕሮፖዛል መሰረት ሥራቸውን በብቃና በጥራት ሊወጡ ይገባል፡፡

ተቋማቱ በፍጥነት ወደ ሥራ በመግባት ለአገር ልማትና ዕድገት የበኩላቸውን በመወጣት አገሪቱ የተያያዘችውን የህዳሴ ጉዞ ሊያፋጥኑ እንደሚገባ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል ገልፀዋል፡፡  

‹‹ልማትን ለማረጋገጥና ሰላምን ለማስፈን መገናኛ ብዙኃን ትልቅ መሳሪያ ናቸው›› ያሉት ሚኒስትሩ ወቅታዊና ሚዛናዊ መረጃዎችን ለህዝቡ ማድረስ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚደረገውን ሽግግር ዕውን ለማድረግም ከቴክኖሎጂው ጋር መራመድ አለባቸው፡፡

ሴት ቶፕ ቦክስ በአገር ውስጥ እንዲመረት መደረጉ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ከማጠናከር በተጓዳኝ ከፍተኛ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ዶክተር ደብረፅዮን አስገንዝበዋል፡፡  የዲጂታል ቴክኖሎጂውን ሽግግር ለማፋጠን ራሱን የቻለ ኮሚቴ ተቋቁሞና የድርጊት መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ እየተሰራ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርዓይ አስገዶም በበኩላቸው መንግስት የግሉ ዘርፍ በመገናኛ ብዙኃን እንዲሳተፍ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩን ገልፀዋል፡፡ በየጊዜውም የግል ብሮድ ካስተሮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው ዛሬ ፍቃድ የተሰጣቸውን ጨምሮ የግል ኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያዎች ቁጥር አስር ደርሷል ብለዋል፡፡

‹‹ሴት ቶፕ ቦክስን ለማምረት ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ ይደረጋል›› ያሉት አቶ ዘርዓይ ይህም ከአምስት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የቴሌቭዥን ባለቤቶች በሽያጭ መዳረስ የሚችል ነው፡፡ አምራቾቹ በዘጠኝ ወራት ወደ ሥራ እንደሚገቡ ጠቁመው ምርቱም በሁሉም አካባቢዎች በተመሳሳይ ዋጋ ለገበያ እንደሚቀርብ ነው ያስገነዘቡት፡፡

ፈቃድ የተሰጣቸው ተቋማት ተወካዮች በበኩላቸው ለህብረተሰቡ ወቅታዊና ሚዛናዊ መረጃዎችን በማቅረብ የመረጃ ክፍተትን ለመሙላት እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡ ህግና ሥርዓትን በመከተል የሙያውን ሥነ ምግባር በማክበር የተሻለ ሥራ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ ሴት ቶፕ ቦክስን ለማምረት ፍቃድ ያገኙት ተቋማትም ጥራቱን የጠበቀ ምርት በማምረት ለገበያ እንደሚያቀርቡ ነው የገለፁት፡፡