ኮማንድ ፖስቱ በሁከት የተሳተፉ በርካታ ግለሰቦች እጃቸውን እየሰጡና የታጠቁትን የጦር መሳሪያ እያስረከቡ መሆናቸውን አስታወቀ ፡፡
በመላው አገሪቱ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስፈፀም የተደራጀው ኮማንድ ፖስት ከህዝቡ እያገኘ ባለው ድጋፍና ትብብር ተጨባጭ ለውጦችን እያመጣ መሆኑን አመልክቷል ።
ኮማንድ ፖስቱ ትናንት ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር፤ ጎንደር ከተማና አከባቢው 93 ሰዎች ለፀጥታ ኃይል እጃቸውን ሰጥተው መግባታቸውን ገልጿል ፡፡
ከእነዚህ ውስጥ 45 ሰዎች ከነሙሉ ትጥቃቸው እና 38 ደግሞ ያለ ትጥቅ የገቡ መሆናቸውን አብራርቷል፡፡
እነዚህ ግለሰቦች ከክልሉ ሸፍተው ጫካ የገቡና ከአሸባሪ ኃይሎች እና ታጣቂዎች ጋር ሲገናኙ እንደነበሩም አመልክቷል ።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የአፈፃፀም መመሪያ በመተላለፍ በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ የንግድ ሱቆቻቸውን በመዝጋት አገልግሎት ለማቋረጥ የተንቀሳቀሱ 13 ነጋዴዎች እና የስራ ማቆም አድማ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሌሎች 13 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ገልጿል ፡፡
እንዲሁም ከትምህርት ገበታ ሆነ ብለው በመቅረት የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማደናቀፍ የሞከሩ ሶስት አስተማሪዎች ህብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ እንደሚገኝ በመግለጫው ጠቁሟል ።
በተመሳሳይ በባህር ዳር ከተማ የንግድ ሱቆቻቸውን በመዝጋት ከተንቀሳቀሱ ውስጥ 29 የንግድ ተቋማት ባለቤቶች ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑን ገልጿል ።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ቄሌም ወለጋ ዞን ደምቢዶሎ ከተማና ሰዶ ወረዳ ዙሪያ ከተለያዩ ቦታዎች ተዘርፈው የተወሰዱ በቁጥር 70 የሚደርሱ የጦር መሳሪያዎች በራሳቸው እና በህብረተሰቡ ጥቆማ ለጸጥታ ኃይሎች ማስረከባቸውን አስታውቋል ።
በቄሌም ወለጋ ዞን ተፈጥሮ የነበረውን ሁከትና ብጥብጥ ሲመሩና ሲያስተባብሩ ከነበሩት ወስጥ እስካሁን 110 ሁከተኞች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ እና ተደብቀው የቀሩትን ሁከተኞች ለመያዝ የክትትል ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቋል።
በክልሉ በህዝብ ንብረትና የልማት ተቋማት ላይ በደረሰው ከፍተኛ ውድመት ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ከነበሩት ውስጥ በምዕራብ አርሲ ወረዳዎች 670 ተጠርጣሪዎች በሻሸመኔ ከተማ 450 በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑም ገልጿል ።
በተመሳሳይ በምእራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ ከተማን ጨምሮ በተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ ከተዘረፈው 162 የጦር መሳሪያዎች ውስጥ በአገር ሽማግሌዎች ጥረት እና በራሳቸው ፈቃድ 88 ያህሉ ተመልሷል ነው ያለው ፡፡
የቀረውን የጦር መሳሪያ እና ከመንግስት፣ ከግልና ከልማት ተቋማት የተዘረፉ ንብረቶችን ለማስመለስ ጥረቱ መቀጠሉን ጠቁሟል ።
ኮማንድ ፖስቱ በምዕራብ ጉጂ ዞን ከተዘረፉት የጦር መሳሪያዎች ውስጥ 32 ክላሺንኮቭ መሳሪያ መመለሱን አስታውቋል ።
በዞኑ በህዝብ ጥቆማና የማጋለጥ ስራ 302 ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ ይገኛል ብሏል መግለጫው ፡፡
በምስራቅ ሸዋ ዞን በአዳማ፣ ቦራ፣ ሎሜ ሊበን ጭቋላ፣ አደአ፣ ቦሰትና አዳሚ ቱሉ በተባሉ ወረዳዎች 92 ዘመናዊ እና ኋላቀር የጦር መሳሪያዎችና 8 ሽጉጦች መያዛቸውን ገልጿል ።
በኦሮሚያ ክልል ከተለያዩ አካላት ከተዘረፈው 513 የተለያየ ዓይነት የጦር መሳሪያዎች ውስጥ እስካሁን ድረስ በተደረገ እንቅስቃሴ 384 ያህሉ መመለሳቸውን አስታውቋል ።
ኮማንድ ፖስቱ ባለፈው አንድ ዓመት በአንዳንድ የአገሪቱ አከባቢዎች ተቀስቅሶ በነበረ ሁከት በቡድን ወይም በግል ወንጀል የፈፀመ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የእርምጃ አፈፃፀም መመሪያ መሰረት በቀሩት አምስት ቀናት ውስጥ በአቅራቢያው ለሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ እጁን እንዲሰጥና የዘረፈውን ንብረት እንዲያስረክብ በድጋሚ አሳስቧል።