አዋጁ ለህዝብ ተሳትፎና ለመንግሥት ተሀድሶ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል-የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለህዝብ ተሳትፎና ለመንግሥት በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ጽህፈት ቤቱ በሣምንታዊ መግለጫው የህዝብ በተለይም የወጣቱን ጥያቄዎች የተለየ ተልዕኮ በነበራቸው የጥፋት ኃይሎች ተጠልፎ ከፍተኛ ጉዳት ወዳደረሱ ጥፋቶች እንዲለወጡ መደረጋቸውን ገልጿል።

እነኚህ እንቅስቃሴዎች ባለፉት ዓመታት ህዝብና መንግሥት ከድህነት ለመውጣት ያመጧቸውን ዕድሎች ማኮላሸት በፈለጉ አካላት የተቀናበሩ እንደነበሩ አስታውቋል።

ይህም ህዝብን ከህዝብ፣ ኃይማኖትን ከኃይማኖት ለማጋጨት እንዲሁም ባለኃብትና ቱሪስቶችን ለማስበርገግ አቅደው የሰሩ የፈረሰችና የተዳከመች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ካላቸው ዓላማ የመነጨ መሆኑን ገልጿል።

በአንፃሩ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት እጅ ለእጅ ተያይዘው በህልውናቸው ላይ የተቃጣውን ጥፋት ማስቆማቸውን መግለጫው አስታውቋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዋና ዓላማ የጥፋት ኃይሎችን በተቀናጀ መልኩ እየተቆጣጠሩ በጥልቀት ለመታደስ የሚያስችል ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሆነ ግልጽ አድርጓል።

በሂደቱም ህዝቡ ተረጋግቶና የተሃድሶ አካል ሆኖ ለመሳተፍና ሠላሙን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት ለማጠናከር የሚያስችል ዕድል እያረጋገጠ ይገኛል ብሏል መግለጫው።( ኢዜአ)