በክልሉ የተጋረጡ ችግሮችን ለመፍታት ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት እንሰራለን – አቶ ለማ መገርሳ

በክልሉ የተጋረጡ ችግሮችን ከህብረተሰቡ ጋር በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ለመፍታት እንደሚሠሩ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሆነው የተሾሙት አቶ ለማ መገርሳ ገለጹ ።

ርዕሰ መስተዳደሩ ለጨፌው አባላት ትናንት ባደረጉት ንግግር እሳቸው እና ካቢኒያቸው በህዝብ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት በትጋት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

አቶ ለማ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫቸውን ይፋ ባደረጉበት ንግግራቸው የክልሉን ሰላም እና ፀጥታ አስጠብቆ የተረጋጋ አውድ መፍጠር ቀዳሚ የትኩረት ማዕከላቸው መሆኑን አንስተዋል።

ይህንንም ለማሳካት ከክልሉ ህዝብ እና ከሚለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ የክልሉን ሰላምና መረጋጋት ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የህዝብ ጥያቄ በየደረጃው የሚመለስ ይሆናልም ነው ያሉት።

እስካሁን የተሰሩ በርካታ ሰራዎች ለክልሉ ትልቅ እድገትን ማምጣታቸውን ያነሱት አቶ ለማ፥ ስራዎቹ የህዝብን እርካታ ከማምጣት አንፃር ብዙ የሚቀር እንዳለ ያሳዩ መሆናቸውን አመላክተዋል።

ከስራ ፈጠራ አንፃር የተሰሩ ስራዎች በየጊዜው ቁጥሩ እየጨመረ ከመጣው ተመራቂ ተማሪና ሥራ ፈላጊ ወጣት ጋር አለመመጣጠኑ በግልፅ የታየ ችግር መሆኑንም ነው የገለፁት።

የወጣቱን ፍላጎት እና ችግር መሠረት ያደረገ የሥራ ፈጠራ መርሃ ግብርን ለመተግበርም ቃል ገብተዋል።

ችግሮችን ቀድሞ መረዳት ለመፍትሄው አቅም ነው ያሉት አቶ ለማ፥ ዛሬ ነገ ሳንል በችግሮቹ መነሻነት ፈጣን ምላሽ ልንሰጥ ይገባል ብለዋል።

ርዕስ መስተዳደሩ ያዋቀሩት ካቢኒ አባላትም የክልሉ መንግስት ትኩረት የሰጠባቸውን መስኮች በአግባቡ በመምራት እና በማስፈፀም ለውጤት ለማብቃት በጨፌው አባላት ፊት ቃል ገብተዋል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)