የሀገርና የህዝብ ፍላጎትን የሚመጥን አመራር ለመፍጠር ጥረት በመደረግ ላይ ነው-መንግስት

የኢፌዲሪ የአዲሱ ዓመት የትኩረት አቅጣጫ ተከትሎ የሀገርና የህዝብ ፍላጎትን የሚመጥን አመራር በየደረጃው ለመፍጠር ጥረት በመደረግ ላይ  መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽሕፈትቤት አስታወቀ ፡፡

ጽሕፈትቤቱ ባወጣው ሳምንታዊ መግለጫ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በቅርቡ በሁለቱ ምክርቤቶች ባደረጉት ንግግር መሰረት ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት ግምገማቸውን የሚመጥን አስፈፃሚ አካልን በድጋሚ ማዋቀር መጀመራቸውን አመልክቷል ።

ክልላዊ መንግስታቱ በካቢኔያቸው ውስጥም በብቃት ሊሰሩ የሚችሉ ምሁራንን በማካተት ላይ መሆናቸውን ገልጿል ።

በተለይም በኦሮሚያ ክልል ሰሞኑን እንደታየው፡ በህገመንግስቱና በህዝብ ፍትኃዊ የልማት ተጠቃሚነት ላይ ዕምነት ያላቸው ዜጎች፡ የገዢው ፓርቲ አባል ወይም ከፍተኛ አመራር መሆን ሳይጠበቅባቸው፡ ህዝባቸውን የሚያገለግሉበትን ዕድል መፍጠሩን ጠቅሷል ፡፡

ሌሎች መንግስትን የመሠረቱ ብሔራዊ ድርጅቶችም በዚሁ ልክ ራሳቸውን በጥልቀት እየፈተሹ ይገኛሉ ብሏል ።

ይህ ሂደት በሀገር አቀፍ ደረጃም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይጠበቃል ነው ያለው ፡፡

የመንግስት ስልጣንን ለህዝብና ለሀገር ጥቅም የማዋል ህዝባዊ ባህሪን ለመመለስና የተገኘውን ዘርፈ ብዙ ስኬት ለማስቀጠል የሚያስችሉ ዝርዝር ተግባራትንም በማከናወን ላይ መሆናቸውን ነው ያስታወቀው ።

ይህን ስርነቀል ለውጥ የሚያረጋግጥ ተሃድሶ ለማደናቀፍ የሚሰሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ኃይሎችን ሴራ በማክሸፍ ህዝብና መንግስት ቀጣይ ጉዟቸውን ለማሳካትም ዘርፈ ብዙ ስራዎችን መስራት ቀጥለዋል ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ በጥረታቸው ያገኟቸውን ዕድሎች ለማስቀጠል በገቡት ቃል መሠረት ሁልጊዜ ለመታረም ክፍት በመሆንና አዳጊ ሁኔታዎችን ለማካተት በመዘጋጀትም ጭምር ተሃድሷቸውን እያጠለቁት እንደሚሄዱ አስገንዝቧል ።

በህዝብ ለመጠየቅ ዝግጁ የሆነ፣ ለህዝብ የሚሠራና ከህዝብ ጋር ለመጠቀም የወሰነ መንግስታዊ መዋቅርን በጠንካራ መሰረትና በአስተማማኝ የህዝብ ተሳትፎ ለመፍጠርና ለማጠናከርም ቀን ከሌት መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጧል።

የመልካም አስተዳደርና ፍትኃዊ ተጠቃሚነት ችግር በመሠረታዊነት እና በአስተማማኝ ሁኔታ የሚፈቱበት አስተሳሰብና የብቃት ደረጃ እስኪፈጠር ድረስም ተቀናጅተው መስራታቸውን ይቀጥላሉ ብሏል ።



ገዥው ፓርቲና መንግስት ራሣቸውን በጥልቀት ለመፈተሽ የገቡትን ቃል ለመፈፀም የተደራጀ ማስፈፀሚያ ዕቅድና ግልፅ ግብ ተቀምጦ ወደ ስራ መገባቱን አስታውቋል ፡፡

መንግስት ህብረተሰቡ ያነሳቸውን የመልካም አስተዳድርና የልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት የተለያዩ ማሻሻዎች በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጾ የተነሱ ጥያቄዎችን መፍታት የሚያስችሉ ያልተማከሉ የአሰራር አደረጃጀቶችን በመዘርጋት ላይ መሆኑንም አመልክቷል።

ህዝብና መንግስት ባለፉት 25 ዓመታት ያስመዝገቧቸውን ስኬቶች ጠብቆ ለማስቀጠል ገዥው ፓርቲና መንግስት ራሳቸውን መፈተሽ፣ ማረምና ህዝባዊ ባህሪያቸውን በድጋሚ ማበልፀግ እንዳለባቸው መግባባት ተፈጥሯል ነው ያለው ፡፡

ለዚሁም ከከፍተኛ አመራሮች ጀምሮም በየደረጃው የሚገኙ አስፈፃሚ አካላት በቂ መግባባት እንዲፈጥሩ እየተደረገ መሆኑን አመልክቷል

ስለሆነም  ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ገዥው ፓርቲና መንግስት ራሳቸውን በጥልቀት እንደሚፈትሹ ዳግም ቃል መግባቱን አስታውሷል ።

መንግስት በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴው ዜጎች የድርሻቸውን የሚወጡበትን እድል የበለጠ እንዲፈጥር የሚሰራ በመሆኑ መላው ህዝብም በጀመረው መንገድ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል ።